ፒዮንግያንግ በቀጣናው ያለውን የኃይል ሚዛን ለማስተካከል እየሰራሁ ነው ብላለች
ተመድ የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ልምምድን እንዲያስቆም ሰሜን ኮሪያ ጠየቀች
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ጥምር ወታደራዊ ልምምድ ባስቸኳይ እንዲያስቆም ጠይቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ ልምምዱ ውጥረቱን እያባባሰ ነው ብሏል።
የአጋሮቹ ልምምዶች እና ንግግሮች ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የግጭቱን ደረጃ እያሳደጉ ናቸው ሲሉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኪም ሶን ጂዮንግ ተናግረዋል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በመጋቢት ወር ከ10 ቀናት በላይ የሚቆይ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምዶችን እንደሚያካሂዱ የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት ተናግረዋል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ልምምዱ እራሳቸውን ለመከላከል እና በሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳይልና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መርሃ-ግብር የወደቀባቸውን ስጋት ለመከላከል አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ ለዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስርዓቶች ውድቀት አሜሪካን ወቅሳለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ፒዮንግያንግ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልማቷ በአካባቢው ያለውን የኃይል ሚዛን ለማስተካከል "ትክክለኛ ምላሽ" ነው ስትል ተናግራለች።
ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኪም "የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ቀስቃሽ አስተያየቶችን እና የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ አጥብቀው መጠየቅ አለባቸው" ብለዋል።
ተመድ "ጠበኛ ተፈጥሮ" ባላቸው ልምምዶች ላይ ያለማቋረጥ ዝም ማለቱ የሚያሳዝን ነው ብለዋልም።
ባለፈው ወር ኪም የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ ላይ “እጅግ ፍትሃዊና ሚዛናዊ ያልሆነ” አቋም አንጸባርቀዋል ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።