ደቡብ ኮርያ እና አጋሮቿ ከሰሜን ኮርያ ጋር ያላቸው ወታደራዊ ፍጥጫ በታሪክ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል- ኪም ጆንግ ኡን
የሰሜን ኮርያው መሪ ከአሜሪካ እና ከደቡብ ኮርያ እየመጣ ያለውን ስጋት ለመመከት ጦሩ በፖለቲካ እና ወታደራዊ አቅም መደራጀት አለበት ብለዋል
ኪም ጆንግ ኡን የሀገራቸው ጦር የውጊያ አቅሙን ለማሳደግ አዳዲስ የመኮንኖች ማሰልጠኛዎች እንዘጋጁ አሳስበዋል
ሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሀገሪቱ ጦር የውጊያ አቅሙን እንዲያሳድግ አሳሰቡ፡፡
በፒዮንግያንግ በተካሄደው የሻለቃ አዛዦች እና የፖለቲካ አስልጣኞች ኮንፈረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር የሀገሪቱ ጦር ሀይል ጦርነትን መቋቋም እንዲችል፤ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ጥንካሬን እንዲያጎለብት እና የውጊያ ቅልጥፍናን እንዲያሳድግ ጠይቀዋል።
“ደቡብ ኮርያን ጨምሮ አሜሪካ እና አጋሮቿ ከሰሜን ኮርያ ጋር ያላቸው ወታደራዊ ፍጥጫ በታሪክ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ ይህም የሰሜን ኮርያን ልሳነ ምድር ትልቁ የፍልሚያ ቦታ አድርጎታል” ያሉት ኪም፤ በሁሉም ወታደራዊ ዘርፍ ወሳኝ ለውጦችን ለማምጣት ሁሉም ርብርብ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን የሀገሪቱ ቴሌቪዥን ኬሲኤንኤ ዘግቧል፡፡
ሻለቃዎችን ለማጠናከር፣ የውጊያ ብቃታቸውን ለማሳደግ እና አሁን ባለው ሁኔታ ዘመናዊ ጦርነት በሚፈለገው መጠን የጦርነት ዝግጅቶችን ለማካሄድ አዳዲስ ወታደራዊ መኮንኖችን ማሰልጠኛ ስፍራዎች እንዲዘጋጁ አዘዋል፡፡
ኪም ጆንግ ኡን ይህን ንግግር ያደረጉት ወደ ሩስያ 10 ሺህ ወታደሮችን ልከዋል በሚል በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ተቃውሞ እና ጫና እየደረሰባቸው በሚገኝበት ወቅት ነው፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮልዲሚር ዘለንስኪ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከሀገራቸው ጦር ጋር ባደረጉት ውጊያ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በመካከላቸው የተካሄዱት የመጀመሪያ ጦርነቶች የአካባቢውን ሰላም እና ደህንነት እንዲሁም የጦርነቱን ሁኔታ የሚቀይረው ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በፔሩ እየተካሄደ በሚገኝው ከእስያ-ፓስፊክ ኢኮኖሚ ትብብር የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል እና የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺገሩ ኢሺባ ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት "በአደገኛ ሁኔታ ለማስፋት" ወስነዋል ሲሉ አውግዘዋል፡
ባለፈው ሳምንት ኪም ኢላማዎች ጋር ተጋጭተው ራሳቸውን የሚያጋዩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ሙከራ ስነስርአት ላይ ተገኝተው መሰል ድሮኖች በጅምላ እንዲመረቱ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
“ሱሳይድ ድሮን” በመባል የሚታወቁት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የማምረት እና የመጠቀም ፉክክር በአለም አቀፍ ደረጃ አሁን አሁን እየጨመረ እንደሚገኝ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፒዮንግያንግ ከደቡብ ኮርያ ጋር የገባችበት ውጥረት ከፍ እያለ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ከሳምንታት በፊት የአህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይል ሙከራዎችን ማድረጓ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን ከሩስያ ጋር በገባችው የመከላከያ እና ደህንነት ትብብር ስምምነት የተለያዩ ዘመናዊ ጦር መሳርያዎችን ምርት ለማጠናከር ማሰቧ ተሰምቷል፡፡