በሩሲያ የሰፈሩት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የወሲብ ፊልሞችን በማየት መጠመዳቸው ተገለጸ
10 ሺህ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት ሰፍረዋል ተብሏል
በስፍራው ያለውን የዩክሬን ወታደሮችን እንዲወጉ ተመድበዋል የተባሉት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ያልተገደበ ኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘታቸው ተገልጿል
በሩሲያ የሰፈሩት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የወሲብ ፊልሞችን በማየት መጠመዳቸው ተገለጸ።
የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን ጨምሮ በርካታ ሀገራት 10 ሺህ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ወደ ሩሲያ መግባታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
የወታደሮቹ ወደ ሩሲያ መምጣት ብዙ ትኩረት የሳበ ሲሆን ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ ዩክሬን እና አሜሪካ ወታደሮቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሲጠይቁ ሰንብተዋል።
የዩክሬን ጦር በተቆጣጠራት የሩሲያዋ ኩርስክ ግዛት የሰፈሩት እነዚህ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ባሳለፍነው ሰኞ ዕለት ስራ ጀምረዋል ተብሏል።
ዘግይቶ በወጣ ዘገባ ደግሞ እነዚህ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች የኢንተርኔት አገልግሎት ሲያገኙ የወሲብ ፊልሞችን በማየት ተደምጠዋል ሲል ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ወታደሮቹ በሀገራቸው የምዕራባዊያንን ባህል እንዳያዩ እገዳ ተላልፎባቸው ቆይቶ ነበርም ተብሏል።
ሰሜን ኮሪያ ወታደሮቿ የወሲብ ፊልሞችን ጨምሮ፣ የምዕራባዊያን ሀገራት ሙዚቃ፣ ባህል ፣ የጸጉር ስታይል እና መሰል የህይወት ዘይቤዎችን ከተገበሩ የሞት ቅጣት ጥላለች።
ይህን ተከትሎ በሩሲያ ያሉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የወሲብ ፊልሞችን በማየት እንደሚያሳልፉ ተገልጿል።
የአሜሪካ መከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል ቻርሊ ዴትዝ ስለ ጉዳዩ ለቀረበላቸው ጥያቄ " ትኩረታችን የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በዩክሬን ጦርነት ላይ ስለሚኖረው ሚና ብቻ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።