"ለማይቀረው ጦርነት የኒዩክሌር ሃይላችን ማጠናከር አለብን" - ኪም ጆንግ ኡን
የሰሜን ኮሪያው መሪ የኒዩክሌር መሳሪያዎችን የሚመረትበትን ተቋም ተዟዙረው ጎብኝተዋል
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከኪም ጋር ሶስት ጊዜ የተገናኙት ትራምፕ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማርገብ እጥራለሁ ብለዋል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሀገሪቱ የኒዩክሌር አቅም እንዲጨምር አዘዙ።
ኪም የኒዩክሌር መሳሪያዎች የሚመረትበትን ተቋም ተዟዙረው ሲጎበኙ "በጣም ጨካኝ ከሆኑ ሀገራት ጋር ጦርነት ውስጥ መግባታችን አይቀሬ ነው፤ ስለዚህ የኒዩክሌር ሃይላችን ማሳደግ አለብን" ማለታቸውን የሀገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ኪም የጎበኙት የኒዩክሌር መሳሪያዎች ማምረቻ የት እንደሚገኝ አልጠቀሰም።
የተለቀቁት ምስሎች ግን ኪም በመስከረም ወር የጎበኙትን የዩራኒየም ማበልጸጊያ ጣቢያ በድጋሚ ሳይመለከቱ እንዳልቀሩ ያሳያሉ ብሏል ሲኤንኤን በዘገባው።
የሰሜን ኮሪያው መሪ በትናንቱ ጉብኝታቸው "የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ማምረት የሚያስችሉ ግብአቶችን የሚያመርቱና የሰሜን ኮሪያን የኒዩክሌር ጋሻ እያጠናከሩ ያሉ" ምሁራን እና ባለሙያዎች አወድሰዋል።
ፒዮንግያንግ ባለፈው ሳምንት እሁድ ስትራቴጂክ ኩርዝ ሚሳኤል መሞከሯን አስታውቃለች።
ከባህር ወደ ምድር እስከ 1 ሺህ 500 ኪሎሜትር የሚምዘገዘገውን ሚሳኤል ያስወነጨፈችው አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በሚያካሂዱት ወታደራዊ ልምምድ መበሳጨቷን ለማሳየት ነበር።
ትራምፕ ዳግም ስልጣን ከያዙ ወዲህ የተደረገው ሙከራ ዋሽንግተን ወደ ድርድር ተመልሳ በፒዮንግያንግ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች እንዲነሱ ጫና ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም ተንታኞች ይገልጻሉ።
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከኪም ጋር ሶስት ጊዜ የተገናኙት ትራምፕ የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማርገብ እጥራለሁ ብለዋል።
የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኪምን "ብልህ ሰው እንጂ አክራሪና የኔን ብቻ ስሙኝ የሚል አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።
በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው የጀመሩትን ንግግር አስቀጥለው ከውጤት ለማድረስና ከኪም ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
የኪም አስተዳደር ከትራምፕ ጋር ለድርድር ሲቀመጥ ከ2018/19ኙ የተሻለ ተጽዕኖ ፈጥሮ ጥቅሙን የማስጠበቅ አቅም አለው፤ ፒዮንግያንግ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ አቅሟ አድጓል፤ ከሞስኮ ጋር ትብብሯም ጠንክሯል።