ሩስያ ኒዩክሌር የታጠቀች ሰሜን ኮሪያ እንድትፈጠር እየሰራች እንደምትገኝ አሜሪካ ገለጸች
ሞስኮ ሰሜን ኮሪያን ከኒዩክሌር መሳርያ ባለቤትነት መከልከል የተዘጋ አጀንዳ ነው ብላለች
የጸጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጉዳይ በጠራው ስብሰባ በሰሜን ምስራቅ እስያ የኒውክሌር ጦርነት ስጋት እያደገ እንደሚገኝ ተገልጿል
ሩስያ የኒዩክሌር ጦር መሳርያ የታጠቀች ሰሜን ኮሪያ እንድትፈጠር እየሰራች መሆኑን አሜሪካ አስታውቃለች፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊናዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ሩስያ የፒዮንግያንግን የኒዩክሌር ጦር መሳርያ ባለቤትነት ከመቀበል ተሻግራ በሂደቱ ውስጥ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡
አምባሳደሯ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳርያ ባለቤት እንዳትሆን ተመድ እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአመታት ያደረጉትን ጥረት ሩስያ ለመቀልበስ እየጣረች ነው ብለዋል፡፡
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ስጋት እና በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ባደረገው ስብሰባ ሩስያ ፣ አሜሪካ እና ሰሜን ኮሪያ ተፋጠው አምሽተዋል፡፡
አምባሳደር ሊንዳ "ሞስኮ የፒዮንግያንግ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ልማትን ለመተቸት ፈቃደኛ ካለመሆን በዘለለ የሰሜን ኮሪያን ጠብ አጫሪ ባህሪ የሚያወግዙ ማዕቀቦች ወይም የውሳኔ ሃሳቦችን ተፈጻሚ እንዳይሆኑ እንቅፋት እየሆነች ትገኛለች” ነው ያሉት፡፡
ባሳለፍነው መስከረም ወር የሩስያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ “የሰሜን ኮሪያ ልሳነ ምድርን ከኒውክሌር ጦር መሳርያ ማጽዳት የሚለው ሀሳብ የተዘጋ አጀንዳ ነው፤ ሀገሪቱ የመከላከያዋን አቅም ለማጠናከር የኒዩክሌር ጦር መሳርያ ባለቤት ለመሆን የምታደርገው ጥረት ምክንያትዊ ነው ብለን እናምናለን” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በወቅቱ ብሪታንያ እና ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ይህን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ሀሳብ በጽኑ አውግዘው አለማቀፋዊ የተረጋጋ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ወደ ኋላ የሚጎትት ነው በማለት ተችተዋል፡፡
በምሽቱ የጸጥታው ምክርቤት ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት በተመድ የሩስያ አምባሳደር ቫዝሊ ኔቤንዚያ የኒዩክሌር ጉዳይን ሳያነሱ በሞስኮ እና በፒዮንግያንግ መካከል እየጠነከረ ስለሚገኘው ከፍተኛ ትችት የሚቀርብበት ወዳጅነት ላይ ምላሽ በመስጠት አተኩረዋል፡፡
አምባሳደሩ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ማንኛውም ሀገር ከሌላው ሀገር ጋር እንደሚያደርገው አለምአቀፍ ህግን የተከተለ ዲፕሎማሲያው ዝምድና እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ በቀጠናው የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር “ጠብ አጫሪ” እንቅስቃሴ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በሰሜን ምስራቅ እስያ የኒዩክሌር ጦርነትን የሚያስከትል ነው ብላለች፡፡
በተመድ የሀገሪቱ አምባሳደር ጆንኮክ ሁዋነግ አሜሪካ የስልጣን ሽግግር በምታደርግበት በመጪዎቹ ወራት ፒዮንግያነግ ትኩረት ለመሳብ ሰባተኛውን የኒውክሌር ጦር መሳርያ ሙከራ አልያም የአህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎችን ልታስወነጭፍ እንደምትችል አሳስበዋል፡፡