የሰሜን ኮሪያው መሪ በሩሲያ ጉብኝት ሊያደርጉ መሆኑ ተነገረ
ኪም ጆንግ ኡን ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በጦር መሳሪያ ሽያጭ ዙሪያ ይነጋገራሉ ተብሏል
አሜሪካ በበኩሏ ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሳሪያ እንዳትሸጥ እያስጠነቀቀች ነው
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በዚህ ወር ወደ ሩሲያ እንደሚያቀኑ ተገለጸ።
ኪም ጆንግ ኡን ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመወያየት ማቀዳቸውንም ሲቢኤስ ቴሌቪዥን የአሜሪካ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ፒዮንግያንግም ሆነች ሞስኮ ስለ ኪም ጉብኝት እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጡም፤ ውይይቱ የሚደረግበት ስፍራም አልተገለጸም።
ኒውዮርክ ታይምስ በበኩሉ ኪም ጆንግ ኡን ወደ ሩሲያ በባቡር ሊጓዙ እንደሚችሉ መረጃዎች ደርሰውኛል ብሏል።
መሪዎቹ ቭላዲቮስቶክ በተባለች ከተማ እንደሚገናኙና የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ሹማምንት ከአንድ ወር በፊት ወደ ከተማዋ በማቅናት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ስለመሆናቸውም ምንጮች ነገሩኝ ብሎ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ለምትገኘው ሩሲያ የጦር መሳሪያ ለማቅረብ የምታደርገው ድርድር በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ዋይትሃውስ በቅርቡ ማሳወቁ ይታወሳል።
በቅርቡ ሰሜን ኮሪያ የድል በዓሏን ስታከበር በፒዮንግያንግ የተገኙት የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉም የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ለሞስኮ የጦር መሳሪያ እንዲያቀርብ አግባብተዋል ነው የተባለው።
ፕሬዝዳንት ፑቲን እና ኪም የሀገራቱን ትብብር ለማሳደግ ቃል የገቡባቸውን ደብዳቤዎች በተከታታይ መላላካቸውንም ነው የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ቃል አቀባዩ ጆን ኪርቢ የተናገሩት።
ፒዮንግያን ለሞስኮ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ የጀመረችው ድርድር እንዲቆም ያሳሰቡት ኪርቢ፥ የጦር መሳሪያ ሽያጩ መካሄዱን ካረጋገጥን በሰሜን ኮሪያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦችን እንጥላለን ብለዋል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያን ያሳሰበው ጉዳይ ሞስኮ በዩክሬን ጦርነት የምታውላቸውን መሳሪያዎች የማግኘቷ ጉዳይ ብቻ አይደለም።
ፒዮንግያንግ ከሞስኮ በምትኩ ምን ታገኛለች? የሀገራቱ ትብብር በእስያ ምን አይነት ፈተና ያመጣል? የሚለውም አሳሳቢ ነው።
ሩሲያ፣ ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ የጋራ የባህር ሃይል ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸውም የዋሽንግተን፣ ሴኡል እና ቶኪዮ ስጋት መሆኑ አልቀረም።
ኪም ጆንግ ኡን ለመጨረሻ ጊዜ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ገጽ ለገጽ የተገናኙት በሚያዚያ ወር 2019 በሩሲያዋ ቭላዲቮስቶክ ከተማ መሆኑ ይታወሳል።