አዲሱ ዘፈን ኪም ጦራቸውንና የተለያዩ ስራዎችን ሲጎበኙ የሚያሳይ ቪዲዮ ተሰርቶለታል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን “የሚያወድሳቸው” አዲስ የሙዚቃ ስራ ይፋ ማድረጋቸው ተነግሯል።
አዲሱ ዘፈን ባሳለፍነው ማክሰኞ የተለቀቀ ሲሆን፤ ዘፈኑ ኪም ጆንግ ኡን የሰሜን ኮሪያ 'ወዳጅ አባት' በማለት ያወድሳል።
አዲሱ ዘፈን ለመጀመሪያ ጊዜ የተለቀቀው በፒዮንግ ያንግ የተገነቡ የ10 ሺህ የመኖሪያ ቤቶች ልማት ምርቃት ላይ እንደሆነም ተነግሯል።
ኪም ጆንግ ኡን የመኖሪያ ቤቶች ምርቃው ስፍራ ከፕሬዝዳንት ፑቲን በሰጣቸው ሊሞዚን መኪና የደረሱ ሲሆን፤ በርካታ የሀገሪቱ ዜጎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በመቀጠልም ከሚመረቁት ህንጻዎቸ በአዱ ፎቅ ላይ የምረቃ ሪባን ለመቁረጥ በተቀመጡበት ቦታ በርካታ ሙዚቀኞች አዲሱን ዘፈን እየዘፈኑ ኪምን የከበቡ ሲሆን፤ የዘፈኑ ርእስም “ወዳጅ አባት” የሚል ነው።
ዘፋኞቹ በአዲሱ ዘፈን የኪም ጆንግ ኡንን ስም ደጋግመው እየጠሩ “የሀገሪቱ የወደፊት ብሩህ ተስፋ” እያሉ ሲያወድሱም ተሰምተዋል።
አዲሱ የኪም ጆንግ ኡን ሙዚቃ ይፋ ሲደረግም ርችቶች የተተኮሱ ሲሆን፤ የኮሪያ ህዝብ አየር ኃይልም አየር ላይ ትርዒት አቅርቧል።
ለኪም ጆንግ ኡን የተዘፈነው አዲሱ ከህንጻ ምረቃው ማግስት ማለትም ረቡዕ በኬ.ሲ.ቲ.ቪ ላይ መለቀቁም ነው የተገለጸው።
ለአዲሱ ዘፈን ቪዲዮ ክሊፕም ተሰርቶለታል የተባለ ሲሆን፤ በቪዲዮ ላይም ኪም ጆንግ ኡን የሀገሪቱን ጦር ሲጎበኙ፣ እንዲሁም የሀገሪቱ ዜጎች ከመቀመጫቸው ቁጭ ብድግ እያሉ ለመሪያቸው ሲያጨበጭቡ ይታያል።