የሰሜን ኮሪያው መሪ ጦራቸው ወታደራዊ ዝግጅቱን እንዲያፋጥን አዘዙ
ኪም ጆንግ ኡን ከአሜሪካ ጋር ያለውን ፍጥጫ የሚመጥን ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት
ደቡብ ኮሪያም ለፒዮንግያንግ ጸብ አጫሪ ድርጊት ፈጣን ምላሽ እሰጣለሁ ብላለች
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሀገራቸው ጦር ወታደራዊ ዝግጅቱን እንዲያጠናክር አዘዙ።
የፒዮንግያንግ የጦር መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች እና የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ሴክተሩም ጭምር ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርግ ነው ያሳሰቡት።
ኪም የአዲስ አመት የትኩረት አቅጣጫቸውን ባመላከተ ንግግራቸው ከአሜሪካ ጋር ያለውን ፍጥጫ የሚመጥን ዝግጅት ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል ብሏል የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ።
ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ዝግጅቷን ከማፋጠን ባሻገር ከ”ጸረ ኢምፔሪያሊስት ነጻ” ሀገራት ጋር ትብብሯን እንደምታጠናክር ነው ኪም ጆንግ ኡን የተናገሩት።
ፒዮንግያንግ ከሞስኮ እና ቤጂንግ ጋር ትብብሯን ማጎልበት የቻለች ሲሆን በ2024ም በምዕራባውያን ከተገፉ ሀገራት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን በንግግራቸው አመላክተዋል።
ሰሜን ኮሪያ ጦሯ በየትኛውም ጊዜ ሊነሳ ለሚችል ጦርነት ዝግጁ እንዲሆን ያስጠነቀቀችው ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ ከ1 ሺህ በላይ ወታደሮች የተሳተፉበት ወታደራዊ ልምምድ ባደረገች ማግስት ነው።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የልም በምስራቃዊ የሀገሪቱ ክፍል ዮንቼን የሚገኙ ወታደሮቻቸውን ሲጎበኙ ከፒዮንግያንግ ለሚቃጣ ማንኛውም ጸብ አጫሪ ድርጊት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ ማሳሰባቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
ፒዮንግያንግ በቅርቡ አህጉር አቋራጭ ሃይፐርሶኒክ ባለስቲክ ሚሳኤል መሞከሯና የስለላ ሳተላይት አምጥቃ ጎረቤቷንና አጋሯን አሜሪካ “እያየኋችሁ ነው” ማለቷ ደቡብ ኮሪያን አሳስቧታል።
ሴኡል ሁለቱን ኮሪያዎች ከሚለየው ድንበር በቅርብ ርቀት መገኘቷም ስጋቱን አንሮታል ነው የተባለው።
አሜሪካም የደቡብ ኮሪያን ስጋት የሚቀንሱ ድጋፎችን ማድረግ መቀጠሏ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት ይበልጥ እያባባሰው እንዳይሄድ ተሰግቷል።