የሰሜን ኮሪያው መሪ ለፍልስጤም ድጋፍ እንዲደረግ ማዘዛቸው ተነገረ
ድጋፉ ለሃማስ የጦር መሳሪያ በማቅረብ ሊታይ እንደሚችልም ነው የደቡብ ኮሪያ የስለላ ተቋም ያስታወቀው
ሃማስ ሰሜን ኮሪያ ሰራሽ መሳሪያዎችን መታጠቁ ሲነገር ሰንብቷል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለፍልስጤማውያን ድጋፍ እንዲደረግ ማዘዛቸውን ደቡብ ኮሪያ ገለጸች።
የሴኡል የስለላ ተቋም ዳይሬክተር ኪም ዩ ዩን ለሀገሪቱ ህግአውጪዎች ባቀረቡት ሪፖርት፥ ፒዮንግያንግ የእስራኤል እና ሃማስን ጦርነት ልትጠቀምበት መዘጋጀቷን ተናግረዋል።
የስለላ ተቋሙ ዳይሬክተር ሰሜን ኮሪያ ለሃማስ እና ሌሎች የጋዛ ታጣቂ ቡድኖች የጦር መሳሪያ ለመሸጥ መዘጋጀቷን መናገራቸውንም ወል ስትሪት ጆርናል አስነብቧል።
የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙሃንም ይህንኑ የዳይሬክተሩን መረጃ ጠቅሰው ጉዳዩን ሰፊ ሽፋን ቢሰጡትም ፒዮንግያንግ ለሃማስ የጦር መሳሪያ ልትሸጥ መሆኑን ያመላክታሉ ያሏቸውን ማስረጃዎች አላቀረቡም።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለፍልስጤማውያን “ሁሉን አቀፍ ድጋፍ” ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ከባለስልጣናቶች ጋር ስለመወያየታቸው ግን በስፋት እየተዘገበ ነው።
ሃማስ ከ25 ቀናት በፊት በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲፈጽም ሰሜን ኮሪያ ሰራሽ መሳሪያዎችን ታጥቆ ታይቷል የሚሉ ዘገባዎች ባለፈው ሳምንት ሲወጡ እንደነበር ይታወሳል።
ቡድኑ ቀደም ብሎም የኪም ጆንግ ኡን ሀገር የሰራቻቸውን የሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና ጸረ ታንክ መሳሪያዎች ታጥቋል የሚሉ ሪፖርቶች ቢወጡም ፒዮንግያንግ ሀሰት ነው በሚል አስተባብላለች።
በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ቴል አቪቭን “የወንጀል ድርጊት እየፈጸመች ነው” ሲትል መውቀሷም አሰላለፏ ከሃማስ ጋር እንደሆነ ያመላክታል የሚሉ ዘገባዎች ሲሰራጩ ቆይተዋል።
የደቡብ ኮሪያው የዜና ወኪል ዮናፕም ለሩሲያ ከ10 መርከብ በላይ የጦር መሳሪያ የላከችው ሰሜን ኮሪያ በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ልትጠቀም እየተዘጋጀች መሆኑን ዘግቧል።
ፒዮንግያንግ በዚህ ወር ሶስተኛውን የስለላ ሳተላይት የማምጠቅ ሙከራ ለማድረግ ከሞስኮ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዳገኘችም የደቡብ ኮሪያን የስለላ ተቋም ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ፒዮንግያንግ ያደረገቻቸው ሁለት የሳተላይት ማምጠቅ ሙከራዎች ሳይሳኩ መቅረታቸው የሚታወስ ነው።