ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ ወታደራዊ መሳሪያ እያቀረበች ነው ስትል አሜሪካ ከሰሰች
ዋሽንግተን ሰሜን ኮሪያ ለሞስኮ አንድ ሽህ በሚሆኑ ኮንቴይነሮች መሳሪያ አቅርባለች ብላለች
ባለፈው ወር የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ወታደራዊ ትብብር ላይ መክረዋል
የአሜሪካ ባለስልጣናት ሰሜን ኮሪያ ለዩክሬን ጦርነት አገልግሎት ላይ የሚውል ከፍተኛ መጠን ያለው ወታደራዊ መሳሪያ ለሞስኮ አቅርባለች ሲሉ ከሰዋል።
የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ ጆን ከርቢ ፒዮንግያንግ በቅርብ ሳምንታት ውስጥ "መሳሪያዎች እና ጥይቶች"ን የያዙ እስከ አንድ ሽህ ኮንቴይነሮችን አቅርባለች ብለዋል።
ቃል አቀባዩ መሳሪያዎቹ በባህርና በባቡር በደቡብ ምዕራብ ሩሲያ በኩል ስለመግባታቸው ተናግረዋል።
ባለስልጣናቱ በሰሜን ኮሪያ ናጂን ውስጥ ለትራንስፖርት የተዘጋጁ ናቸው ያሏቸውን 300 ኮንቴነሮች ምስል ይፋ አድርገዋል።
የአሜሪካ ደህንነት መሳሪያዎቹ ከጎርጎሮሳዊያኑ መስከረም 7 እስከ ጥቅምት 1 ድረስ ሩሲያ እጅ ገብተዋል ብሏል።
ባለፈው ወር የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሩሲያን ጎብኝተው ስለ ወታደራዊ ትብብር መምከራቸው ይታወሳል።
የሞስኮ ጦር ከፍተኛ መጠን ያላቸው መሳሪያዎች እየተመናመነ እንደሚገኝ የታመነ ሲሆን፤ ሩሲያ ከአንዳንድ አጋሮቿ አቅርቦቱን ለመሙላት ስትፈልግ መቆየቷን ቢቢሲ ዘግቧል።
አንዳንድ ተንታኞች ኪም ጆንግ ኡን ከፍተኛ የመሳሪያ ክምችት እንዳላቸው ይናገራሉ።
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ጀምሮ ዋሽንግተን ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ መሳሪያ እያቀረበች ነው በሚል በተደጋጋሚ ከሳለች።