ሰሜን ኮሪያ፣ ቻይና እና ሩሲያ ቀጣናዊ ውጥረትን የማርገብ ፖሊሲን እየተከተሉ መሆኑን ሞስኮ ገለጸች
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ሰሜን ኮሪያ ሀገራቸው በዩክሬን የምታደርገውን 'ወታደራዊ እርምጃ' በመደገፏ አመስግነዋል።
ሞስኮ ለሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን "ሙሉ ድጋፍ እና አጋርነት" እንደምትሰጥም ቃል ገብታለች።
ላቭሮቭ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በፖለቲካ ከተገለለችው ሰሜን ኮሪያ ጋር ትብብርን ለማጠናከር ለሚያደርጉት ጉብኝት ሜዳውን ለማመቻቸት ረቡዕ ዕለት ፒዮንግያንግ ገብተዋል።
ላቭሮቭ ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ላለችው "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ" የፒዮንግያንግን "የማያወላውል" ድጋፍ ታደንቃለች ብለዋል።
"በተመሳሳይ የሩስያ ፌዴሬሽን ለሰሜን ኮሪያ ያለውን ድጋፍ እና አጋርነት ያሳያል" ሲሉ በሚንስቴሩ ድረ-ገጽ በተለቀቀ ንግግራቸው ገልጸዋል።
ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ቾ ሶን ሁይ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ላቭሮቭ ለጋዜጠኞች የአሜሪካና የአጋሮቿ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መጨመር አሳሳቢ ነው ብለዋል።
ላቭሮቭ እንደተናገሩት ሰሜን ኮሪያ፣ ቻይና እና ሩሲያ ቀጣናዊ ውጥረትን የማርገብ ፖሊሲን እየተከተሉ ነው።
የሰሜን ኮሪያ የመንግስት መገናኛ ብዙኸን የላቭሮቭ ጉብኝት በፒዮንግያንግ እና በሞስኮ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር "ትልቅ አጋጣሚ" ነው ብለዋል።