የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ጥምረት ምዕራባዊያንን ማስፈራቱ ተገለጸ
ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ዩክሬን እና አሜሪካ የሁለቱ ሀገራት አዲስ ግንኙነት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል
ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ መረጃዎችን ልትሰጥ እንደምትችል ተሰግቷል
የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ጥምረት ምዕራባዊያንን ማስፈራቱ ተገለጸ፡፡
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን ከሰሞኑ ወደ ሞስኮ አቅንተው ሩሲያን ጎብኝተው ተመልሰዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከመምከራቸው ባለፈ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ ማዕከላትን እና ማምረቻ ቦታዎችን ጎብኝተዋል፡፡
የሑለቱ ሀገራት መሪዎች ከመከሩባቸው ጉዳዮች መካከል ወታደራዊ ትብብሮች፣ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የምግብ ዋስትና ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን ሰሜን ኮሪያን እንዲጎበኙ ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን ግብዣውን ስለመቀበላቸውም ተገልጿል፡፡
ይህን የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ሰፊ ውይይት ተከትሎም በርካታ የምዕራባዊን እና እስያ ሀገራት ጉዳዩ እንዳሳሰባቸው እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲወያይበት ጥያቄ አቅርበዋል ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲንና የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን የመኩሩባቸው አንኳር ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?
ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ዩክሬን ፣ አሜሪካ እና ሌሎችም ስማቸው ያልተጠቀሱ የአውሮፓ ሀገራት የፕሬዝዳንት ፑቲን እና ኪምን ውይይት በጥርጣሬ እንዳዩት ሲኤንኤን ምሁራንን አነጋግሮ ዘግቧል፡፡
ይሁንና የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ዋነኛ የንግድ አጋር የሆነችው ቻይና ግን የሁለቱን መሪዎች ውይይት በመልካም እና በጠቃሚነት ትመለከተዋለች ተብሏል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ለጀመረችው ጦርነት የተተኳሽ እጥረት እንዳያጋጥማት ሰሜን ኮሪያ ጥሩ የግብዓት ምንጭ ትሆናታለች የተባለ ሲሆን ሰሜን ኮሪያም በማዕቀብ ምክንያት ለተጎዳው የሚሳኤል ልማት ስራዎቿ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከሞስኮ በቀላሉ ልታገኝ እንደምትችል በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ ሩሲያን የጎበኙት የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡንን በጠላትነት ዝርዝር ውስጥ መዝግባቸዋለች፡፡