ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያው መሪ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎቿን አስጎበኘች
ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በሩሲያ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ኪም ጆንግ ኡን፥ የሞስኮን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችም ተመልክተዋል
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ወታደራዊ ትብብር ዋጋ ያስከፍላል እያሉ እየዛቱ ነው
ሩሲያ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎቿንና ኒዩክሌር ተሸካሚ አውሮፕላኖቿን ለሰሜን ኮሪያው መሪ አስጎበኘች።
ኪም ጆንግ ኡን ከቭላዲቮስቶክ ከተማ በ40 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አርይቶም ከተማ ጉብኝት እያደረጉ ነው።
የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉም “ኪንዝሃል” የተሰኘውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ለኪም አስጎብኝተዋል።
የኒዩክሌር እና የሌሎች መሳሪያዎች አረር መሸከም የሚችለው “ኪንዝሃል” ከ1 ሺህ 500 እስከ 2 ሺህ ኪሎሜትሮች በመምዘዝገግ ኢላማውን ማደባየት ይችላል ተብሏል።
ኪም ሶስት አይነት ሞዴል ያላቸውን ቦምብ ጣይ የጦር አውሮፕላኖችም እንዲጎበኙ መደረጉን የሩሲያው ኢንተርፋክስ ዘግቧል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ሚሳኤሎች ከጦር አውሮፕላኖቹ ላይ እንዴት እንደሚተኮሱ ጠይቀውም የሩሲያ ወታደራዊ ባለስልጣናት ማብራሪያ ሲሰጧቸው የሚያሳይ ምስል ተለቋል።
በአረንጓዴ ባቡራቸው ባለፈው ረቡዕ ሩሲያ የገቡት ኪም ጆንግ ኡን በትናንትናው እለትም ኮምሶሞልስክ በተባለችው ከተማ የሩሲያን የጦር ጄቶች ማምረቻ መጎብኝታቸው የሚታወስ ነው።
የኪም የሩሲያ ጉብኝት ፒዮንግያንግ የአየር ሃይሏን ለማዘመን የያዘችውን እቅድ ያሳያል፤ ለዚህም ከሞስኮ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ይጠበቃል ብለዋል ተንታኞች።
ሰሜን ኮሪያ በኒዩክሌር ፕሮግራሟ አለምን ብታስጨንቅም የምትጠቀማቸው የጦር አውሮፕላኖች በ1980ዎቹ በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት የተላኩላት ናቸው።
ኪም ጆንግ ኡን በዛሬው እለትም በቭላዲቮስቶክ ከተማ የሚገኘውን የሩሲያ ባህር ሃይል ይጎበኛሉ ተብሏል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የኪም ጆንግ ኡን የሚሳኤሎች እና የጦር አውሮፕላኖች ጉብኝት ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንድታገኝ ሊያደርጋት እንደሚችል ገልጸዋል።
ፒዮንግያንግ በምትኩም ሞስኮ በዩክሬን ለምታደርገው ጦርነት መሳሪያ ትልካለች የሚል ስጋት አላቸው።
ኪም ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር በነበራቸው ምክክር የዩክሬኑ ጦርነት አንዱ አጀንዳ እንደነበር ይፋ ቢደረግም ሞስኮ በመንግስታቱ ድርጅት የተጣሉ ክልከላዎችን ተላልፋ ከሰሜን ኮሪያ መሳሪያዎችን እንደማትወስድ ፑቲን ለጋዜጠኞች መናገራቸው የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጂ ኪም ጆንግ ኡን ሩሲያ ከምዕራባውያን ጋር የምታደርገውን ጦርነት “ቅዱስ ጦርነት” ነው ማለታቸውና ሀገራቸው ኢምፔሪያሊዝምን ለማጥፋት ከሩሲያ ጋር እንደምትተባበር መግለጻቸው አይዘነጋም።
ዋሽንግተን እና አጋሮቿ ይህ የፒዮንግያንግ አቋም ዋጋ ያስከፍላታል እያሉ እየዛቱ ይገኛሉ።