ፖለቲካ
የሰሜን ኮሪያው ኪም በ2022 እቅድ ስለምግብ እንጅ ስለኑክሌር አለማንሳታቸው ተገለጸ
ኪም ከደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ፋላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል
የሰሜን ኮሪያው ኪም በ2022 የኮሪያ ዋና ግብ የኢኮኖሚ እድገትና የሰዎችን ኑሮ ማሻሻል ነው ብለዋል
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ኪም በኮሪያው የሰራተኛ ፓርቲ የመጨረሻ ስብሰባ ላይ በ2022 የኮሪያ ዋና ግብ የኢኮኖሚ እድገትና የሰዎችን ኑሮ ማሻሻል መሆኑንና ይህም የህይወት እና የሞት ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ኪም ይህን ያሉት ሰኞ እለት በጀመረው 8ኛው የኮሪያ የሰራተኞች ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነው።
የአምስት ቀናቱ ስብሰባ፤ በ2011 አባቱ ከሞቱ በኋላ ኪም የሀገሪቱን መሪነት በተሳካ ሁኔታ ከያዙ 10ኛ ዓመታት ጋር ተገጣጥሟል፡፡
ኪም ከደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ጋር ጉልህ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመሩን ጨምሮ ዋና ዋና የፖሊሲ ለውጦችን ለማድረግ ከአዲሱ ዓመት ቀደም ብለው ባደረጓቸው ንግግሮች ጠቅሰዋል፡፡
ነገር ግን በሰሜን ኮሪያ የመንግስት ሚዲያ ላይ የታተመው የንግግራቸው ማጠቃለያ ስለ አሜሪካ የተለየ ነገር አላነሳም፡፡ ኪም አብዛኛውን ንግግራቸውን የሀገር ውስጥ ጉዳዮችን፣ ከገጠር ልማት ትልቅ እቅድ እስከ የሰዎች አመጋገብ፣ የትምህርት ቤት ዩኒፎርም እና "የሶሻሊስት ያልሆኑ ድርጊቶችን" የመቆጣጠር አስፈላጊነትን በመዘርዘር ማጠቃለላቸው ተገልጿል፡፡