የሰሜን ኮሪያው መሪ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎችን ጎበኙ
ኪም ጉብኝቱን ያደረጉት 50 ሀገራት ሩሲያ በዩክሬን የሰሜን ኮሪያን ባለስቲክ ሚሳኤሎች መጠቀሟን ባወገዙ ማግስት ነው
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በዛሬው እለት በሞስኮና ፒዮንግያንግ ወታደራዊ ትብብር ዙሪያ ይወያያል ተብሏል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የጦር መሳሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎችን ጎበኙ።
ኪም ተንቀሳቃሽና አጭር ርቀት ሚሳኤል ማስወንጨፊያ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ተዟዙረው መጎብኝታቸውን የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
በጉብኝታቸው ወቅትም “ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያላቸው ወሳኝ የጦር መሳሪያዎች” በብዛት እንዲመረቱና የአቅጣጫ ለውጥ እንዲደረግ ማሳሰባቸውን ነው የተገለጸው።
የሰሜን ኮሪያው መሪ የጦር መሳሪያ ፋብሪካዎቹን መጎብኘታቸው ዜና የተሰማው 50 ሀገራት ፒዮንግያንግ ለሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን መሸጧን ባወገዙ ማግስት ነው።
ሀገራቱ ሞስኮ በዩክሬኑ ጦርነት የሰሜን ኮሪያን ባለስቲክ ሚሳኤሎች መጠቀሟንና ሌሎች ቴክኒካዊ ድጋፎችን ማግኘቷን በመጥቀስ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የዋይትሃውስ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ጃክ ሱሊቫኒ ወደ ደቡብ ኮሪያው አቻቸው ቻንግ ሆ ጂን ደውለው ፒዮንግያንግ ወደ ሞስኮ ሚሳኤሎችን መላኳን በጽኑ መቃወማቸውም ተገልጿል።
ሩሲያ የሰሜን ኮሪያን ባለስቲክ ሚሳኤል መጠቀም መጀመሯ የተነገረው በ2023 ታህሳስ ወር መጨረሻ ሲሆን፥ በዩክሬኗ ካርኬቭ ከተማ የወደቀው ሚሳኤል ሰሜን ኮሪያ ሰራሽ መሆኑ መረጋገጡን የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት ምክርቤት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ተናግረዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በዛሬው እለት በሚያደርገው ስብሰባም የሰሜን ኮሪያ ባለስቲክ ሚሳኤል በዩክሬኑ ጦርነት ጥቅም ላይ የመዋሉ ጉዳይ አንዱ አጀንዳ ይሆናል ነው የተባለው።
ሰሜን ኮሪያም ሆነች ሩሲያ ግን በምዕራባውያኑ እየቀረበባቸው ለሚገኘው ወቀሳ ምላሽ አልሰጡም።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከሁለት ሳምንት በፊት በሰሜን ኮሪያ ድንበር ልምምድ ማድረጋቸው ያስቆጣት ፒዮንግያንግ “ለማይቀረው ጦርነት” መዘጋጀትን መርጣለች።