ሴኡል ሚሳዔል የተኮሰችው ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው
ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ጠዋት ላይ በጣም ኃለኛ የተባለ የባላስቲክ ሚሳዔል መተኮሷ ተነገረ።
ፒዮንግያንግ ሚሳዔል የተኮሰችው ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ የሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር ጥቃት ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።
የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ሰሜን ኮሪያ እጅግ ዘመናዊ የረዥም ርቀት ሚሳኤል መተኮሷን ያረጋገጡ ሲሆን፤ ተግባሩም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እገዳዎችን የጣሰ ነው ብለዋል።
ወደ ጃፓን ባህር የተተኮሰው አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔሉ በሆካይዶ ባህር ምእራባዊ ክፍል ላይ የወደቀ ሲሆን፤ ከምእራቡ ዓለም ከፍተኛ ውግዘትን እያስተናገደ ነው።
የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ የመከላከያ ባለስልጣናት ከሰሜን ሊደስር ለሚችለው የኒውክሌር ጥቃት ምላሽ ለመስጠት እቅዳቸውን ለማሻሻል ተገናኝተው መወያያቸው ይታወሳል።
ፒዮንግያንግ ስብሰባውን ተከትሎ ባወጣችው መግለጫ “የበለጠ ከባድ የመከላከያ እርምጃዎችን” እንደምትወስድ ተናግራለች።
የዛሬው የሚሳዔል መተኮስም ለዚሁ ምላሽ ነው የተባለ ሲሆን፤ የረጅም ርቅት የባላስቲክ ሚሳዔሉ ዛሬ ጠዋት 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ገደማ ነው የተተኮሰው።
የደቡብ ኮሪያ እና የጃፓን ባለስልጣናት እንደረጋገጡት ከሆነ የሰሜን ኮሪያ ሚሳዔል ለ73 ደቂቃዎች የተጓዘ ሲሆን፤ 1,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ተወንጭፏል።
አሁጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳዔሎች አሜሪካን የመምታት አቅም ያላቸው ሲሆን፤ ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ያካሄደችው የማስወንጨፍ ስነስርዓት 5ኛው የተሳከ ሙከራ እንደሆነም ታውቋል።