የትራምፕ አስተዳደር ጸብ የማጫሩን ድርጊት ገፍቶበታል - ኪም ዮ ጆንግ
የሰሜን ኮሪያው መሪ እህት አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የባይደን አስተዳደርን "የጥላቻ ፖሊሲ" በማስቀጠሉ ፒዮንግያንግ የኒዩክሌር ሃይሏን ማጠናከር አለባት ብለዋል

ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ የኪም አስተያየት ሰሜን ኮሪያ ለምትካሂደው የኒዩክሌር መሳሪያ ልማት መሸፈኛ ሰበብ ፍለጋ ነው በሚል ውድቅ አድርጋዋለች
የሰሜን ኮሪያው መሪ እህት ኪም ዮ ጆንግ አዲሱን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ"ጸብ አጫሪነት" ከሰሱ።
ከኪም ጆንግ ኡን ቀጥሎ ከፍተኛ ስልጣን እንዳላቸው የሚነገርላቸው ኪም ዮ ጆንግ "አዲሱ አስተዳደር ስልጣን ከያዘ በኋላ አሜሪካ በሰሜን ኮሪያ ላይ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቁስቆሳዋን ገፍታበታለች" ማለታቸውን የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
"(ትራምፕ) የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ባይደን የጥላቻ ፖሊሲ አስቀጥለዋል፤ ይህም ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር ጦርነት እንዳይጀመር የመገዳደር ሃይሏን የሚጨምር ስራዋን መግፋት እንዳለባት ያሳያል"ም ነው ያሉት።
ኪም ዮ ጆንግ አሜሪካ "ዩኤስኤስ ካርል ቪንሰን" የተሰኘችውን አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ከትናንት በስቲያ እሁድ ወደ ደቡብ ኮሪያ መላኳንም ፒዮንግያንግን ለግጭት ለመቀስቀስ ያለመ ነው በሚል ተቃውመውታል።
አሜሪካ በቅርቡ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ታደርጋለች።
የሀገራቱን ወታደራዊ ልምምድ "የወረራ ዝግጅት ነው" በሚል የምትቃወመው ፒዮንግያንግ ባለፈው ሳምንት ስትራቴጂክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን በመሞከር እንደተለመደው ተቃውሞዋን በሚሳኤል ገልጻለች።
የኪም ጆንግ እህት አሜሪካ በሶስትዮሽ ወታደራዊ ልምምዱ የሚሳተፉ "ቢ-1ቢ" ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖችን ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር መላኳንና በየካቲት ወር በጀርመን በተካሄደው የሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ሰሜን ኮሪያን የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንዳትሆን የደረሱትን ስምምነትም ተችተዋል።
የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የኪም ዮ ጆንግ አስተያየት ሰሜን ኮሪያ ለምትካሂደው የኒዩክሌርና ሚሳኤል ልማት መሸፈኛ ሰበብ ፍለጋ ከመሆን ውጭ ትርጉም የለውም ብሏል።
"ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤትነት ተቀባይነት የለውም፤ ሀገሪቱ ህልውናዋ እንዲቀጥል ብቸኛው አማራጯ ከኒዩክሌር (መሳሪያ) አባዜ እና ቅዠቷ መውጣት ነው" ሲልም አክሏል።
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን ለማርገብ የሞከሩት ዶናልድ ትራምፕ ከኪም ጆንግ ኡን ጋር በአካል መገናኘታቸውና የሁለቱን ኮሪያዎች መሪዎች ማጨባበጣቸው ይታወሳል።
ትራምፕ ከኪም ጋር ተከታታይ ምክክሮችን ቢያደርጉም ውጥረቱን ሳያረግቡ የስልጣን ዘመናቸው አክትሞ ነበር።
በጥር ወር ዳግም ወደ ነጩ ቤተመንግስት የገቡት የ78 አመቱ ፕሬዝዳንት ከሰሜን ኮሪያው መሪ ጋር ዳግም እንደሚገኙ መግለጻቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።