ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካና አጋሮቿን የኑክሌር ትጥቅ እናስፈታለን ዛቻ "የማይረባ" ስትል አወገዘች
የደቡብ ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሜን ኮሪያ በድብቅ እያካሄደች ያለውን የጦር መሳሪያ ፕሮግራም እንድታቆምና የኑክሌር ትጥቋን ወደመፍታት እንድትመለስ አሳስቧል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/18/243-155604-img-20250218-145225-344_700x400.jpg)
የሶስቱ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በሙኒክ ከተማ ባደረጉት ስብሰባ የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ትጥቅ ለማስፈታት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል
ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካና አጋሮቿን የኑክሌር ትጥቅ እናስፈታለን ዛቻ "የማይረባ" ስትል አወገዘች።
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን በቅርቡ ያቀረቡትን የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ትጥቅ እናስፈታለን ዛቻ ያወገዙት የሰሜን ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገሪቱ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ማልማቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል በዛሬው እለት መናገራቸውን ሮይተርስ ኬሲኤንኤንን ጠቅሶ ዘግቧል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ፣ የደቡብ ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾ ታይ ዩኡልና የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እዋያ ታከሽ በጀርመን ሙኒክ ከተማ ከተካሄደው የጸጥታ ስብሰባ ጎን ለጎን ባለፈው ቅዳሜ ባደረጉት ወይይት የሰሜን ኮሪያን የኑክሌር ትጥቅ ለማስፈታት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገራቱን "ያለፈበት፣ የማይረባ" እቅድ በማራመድ ተችተው፣ ቀጣናዊ ግጭት የሚቀሰቅስ ነው ብለዋል።
"አሜሪካና አጋሮቿ የደቀኑት ስጋት እስካለ ድረስ፣ የዲፒአርኬ (የሰሜን ኮሪያ) ኑክሌር ኃይል ራስን ለመከላከልና እንዲሁም ሰላምና ሉአላዊነትን ለማስከበር ይውላል" ሲል ኬሲኤንኤ በስም ያልጠቀሰውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጠቅሶ ዘግቧል።
የደቡብ ኮሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሜን ኮሪያ በድብቅ እያካሄደች ያለውን የጦር መሳሪያ ፕሮግራም እንድታቆምና የኑክሌር ትጥቋን ወደመፍታት እንድትመለስ አሳስቧል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ሊ ጃይ ውንግ "ሰሜን ኮሪያ ኑክሌር የታጠቀች ሀገር ሆና በፍጽም እውቅና የሚገባት ሀገር አይደለችም" ብለዋል።
"የኑክሌር ጦርና ሚሳይል መሳሪያ ልማት የራሳቸውን ጸጥታና የኢኮኖሚ ልማት ያደናቅፋል ብለው እንደሚረዱ ተስፋ እናደርጋለን።"
የሶሰቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ባልተጠበቀ ሁኔታ ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር የተገናኙት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ በዓለ ሲመታቸውን ከፈጸሙ በኋሃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነው።
በብሔራዊ ደህንነት አገልግሎት መረጃ የተሰጣቸው የሰሜን ኮሪያ ህግ አውጭዎች የቅረቡ የሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ "የመከላከል አቅሟን ለማሳየትና የትራምፕን ትኩረት ለመሳብ ነው"ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያ ጦርም በቅርቡ በሀገር ውስጥ የተሰራ ኮሪያን ታክቲካል ሰርፌስ ቱ ሰርፌስ(ኬቲኤስኤስኤም) ወይም ከአየር ወደ አየር የሚተኮስ ከምድር ስር ያለ ምሽግን ለመስበር የሚያስችል ሚሳይል መስራቷን ይፋ አድርጓል። ይህ መሳሪያ የሰሜን ኮሪያን የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያ ስርዓት ያለበትን ብታ መምታት የሚችል ነው ተብሏል።