ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ወታደሮችን ወደ ሩስያ መላኳን የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት አስታወቀ
የስለላ ተቋሙ በሁለተኛው ዙር ምን ያህል ወታደሮች ወደ ሩስያ እንደተላኩ እያጣራሁ ነው ብሏል

ፒዮንግያንግ ከዚህ ቀደም ቁጥራቸው ከ10-12 ሺህ የሚደርሱ ወታደሮችን መላኳን አሜሪካ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል
የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ወታደሮቿን ወደ ሩሲያ መላኳን አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ የመረጃ አግልግሎት (ኤን አይ ኤስ) የተባለው የደቡብ ኮሪያ የሰለላ ተቋም ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ ወታደሮችን የላከችው ቀደም ሲል በውግያ ግንባሮች ላይ የተሰማሩ ወታደሮች ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ነው ብሏል፡፡
ኤንአይኤስ ተጨማሪ የተላኩት የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በየካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ውስጥ በሩሲያ ከርስክ ግዛት ላይ እንዲሰማሩ መደረጉን መረጃዎች ማግኘቱን ነው የገለጸው፡፡
ሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ መጠን ያለው የጦር መሳሪያ ለሩሲያ እያቀረበች እንደምትገኘ እና ከ10-12 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን ወደ ሩሲያ መላኳን የአሜሪካ፣ የደቡብ ኮሪያ እና የዩክሬን የስለላ ባለስልጣናት አስታውቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ወታደራዊ ተንታኞች የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች ከፍተኛ ዲሲፕሊን የተላበሱ እና ጥሩ ወታደራዊ ስልጠና ያላቸው እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
ነገርግን በውጊያ ልምድ ማነስ እና አካባቢውን ባለማወቃቸው በሩስያ-ዩክሬን የጦር ግንባሮች ላይ የድሮን እና የመድፍ ጥቃት ኢላማ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የደቡብ ኮሪያ የስለላ ድርጅት በጥር ወር ወደ 300 የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች መሞታቸውን እና ሌሎች 2700 የሚሆኑት ደግሞ መቁሰላቸውን አሳውቋል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው በከርሰክ ግዛት የሞቱ እና የቆሰሉ ሰሜን ኮሪያውያን ቁጥር 4 ሺህ እንደሚጠጋ ቢገልጹም አሜሪካ ቁጥሩ 1200 ገደማ እንደሆነ ተናግራለች፡፡
የደቡብ ኮሪያው ጁንግአንግ ኢልቦ ጋዜጣ ማንነታቸው ያልታወቁ የመንግስት ምንጮችን በመጥቀስ በትላንትናው ዕለት እንደዘገበው ተጨማሪ 3 ሺህ የሚጠጉ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በጥር እና በየካቲት ወር በከርስክ ግዛት ተሰማርተዋል።
ደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ እና አጋሮቻቸው ሩሲያ የሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራም በእጅጉ ሊያሳድጉ የሚችሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን ልትሰጥ እንደምትችል ስጋት አላቸው፤ በተጨማሪም ፒዮንግያግ ከሞስኮ ኢኮኖሚያዊ እና ሌሎች ድጋፎችን እያገኘች እንደምትገኝ ይገልጻሉ፡፡
ይሁንና ሩስያ እና ሰሜን ኮሪያ ይህን የምዕራባውያን እና የደቡብ ኮሪያ ክስ ከእውነት የራቀ መረጃ ነው ሲሉ በተደጋጋሚ አስተባብለዋል፡፡