ኪም ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር መሳሪያዋን ለመጠቀም በሙሉ አቅሟ እንድትዘጋጅ አሳሰቡ
ፒዮንግያንግ በኮሪያ ልሳነ ምድር ምዕራባዊ ክፍል በርካታ ስትራቴጂክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ሞክራለች

አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ "የነጻነት ጋሻ" የሚል ስያሜ የሰጡትን ወታደራዊ ልምምድ በቀጣዩ ወር ይጀምራሉ
ሰሜን ኮሪያ ሁሉንም የኒዩክሌር መሳሪያዋን ለመጠቀም በሙሉ አቅሟ እንድትዘጋጅ የሀገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን አሳስበዋል።
ኪም ሀገራቸው በርካታ ስትራቴጂክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ስታስወነጭፍ ከተመለከቱ በኋላ ነው ይህን ያሉት።
ክሩዝ ሚሳኤሎቹ ለ130 ደቂቃዎች 1 ሺህ 587 ኪሎሜትሮችን ከተምዘገዘጉ በኋላ የተቀመጠላቸውን ኢላማ መምታታቸውን የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ኬሲኤንኤ ዘግቧል።
የሚሳኤል ሙከራው "ደህንነታችን እየተፈታተኑ ለሚገኙ ለጠላቶቻችን የመልሶ ማጥቃት አቅማችን ምን ላይ እንደደረሰ አሳይቷል" ብለዋል መሪው ኪም ጆንግ ኡን።
"ጠንካራ የማጥቃት አቅም ዋነኛው መገዳደሪያ እና የመከላከያ መንገድ ነው" ያሉት ኪም ጆንግ ኡን፥ የሰሜን ኮሪያ ጦር የኒዩክሌር ታጣቂ ሃይል የአውደ ውጊያ ዝግጁነቱን እየፈተሸ መሳሪያዎቹን ጥቅም ላይ ለማዋል ሰፊ ዝግጅት እንዲያደርግ ማሳሰባቸውም ተገልጿል።
የክሩዝ ሚሳኤሎች ሙከራው በምዕራባዊ የኮሪያ ልሳነ ምድር የባህር ዳርቻ "ቢጫ ባህር" ላይ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ መከናወኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ፒዮንግያንግ ባለፈው ረቡዕ ሚሳኤሎችን ለማስወንጨፍ ስትዘጋጅ እንደነበር ማወቁን ከመግለጽ ውጪ እንደከዚህ ቀደሙ ዝርዝር መግለጫ አላወጣም።
ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር አረር የሚገጠምላቸው ስትራቴጂክ ክሩዝ ሚሳኤሎችን በብዛት በማምረት ላይ ትገኛለች።
ክሩዝ ሚሳኤሎች በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሃሳቦች በይፋ የታገዱ በመሆኑ እንደ ባለስቲክ ሚሳኤል ስትሞክር የሚደርስባት አይነት አለማቀፍ ተቃውሞ አላስከተለባትም።
የጸጥታው ምክርቤት በሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳኤል እና የኒዩክሌር ጦር መሳሪያ ልማት ላይ ያነጣጠሩ በርካታ ማዕቀቦችን መጣሉ የሚታወስ ነው።
የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር በስም ከማይጠቅሷቸው "ጠላቶች" ለሚቃጣ ጥቃት ከፍተኛ የማጥቃት አቅም ያላቸው ስትራቴጂክ ክሩዝ ሚሳኤሎች ሙከራ እንዲቀጥል አዘዋል።
ጎረቤት ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ በቀጣዩ ወር የሚጀምሩትን "የነጻነት ጋሻ" የሚል መጠሪያ ያለው አመታዊ ወታደራዊ ልምምድ ተከትሎም የፒዮንግያንግ የሚሳኤል ሙከራ ይደጋገማል ተብሎ ይጠበቃል።
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከኪም ጋር ደጋግመው የተገናኙት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግን ውጥረቱን ለማርገብ እንደሚሰሩ መግለጻቸው ይታወሳል።