“ከተሰጠኝ ኃላፊነት የመነሳቴ ነገር ከትሮንቮል ጋር መገጣጠሙ አስገርሞኛል”- ክንደያ ገብረህይወት (ፕ/ር)
ዩኒቨርስቲውን ላለፉት 8 ገደማ ዓመታት ያገለገሉት ፕሮፌሰሩ ከነገ ጀምሮ ቀደም ሲል በነበራቸው ኃላፊነት እንደማይቀጥሉም ታውቋል
ፕሮፌሰሩ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትነታቸው መነሳታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል
ክንደያ ገብረህይወት ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንትነታቸው ተነሱ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ክንደያ ገብረህይወት (ፕ/ር) ከሃላፊነት መነሳታቸውን አስታወቀ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ ለነበራቸው አበርክቶ ያመሰገኑት ሚኒስትሩ ሳሙዔል ኡርካቶ (ዶ/ር) ከነገ ጀምሮ መስከረም 5 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ የተሰጣቸው ኃላፊነት መነሳቱን በጻፉት ደብዳቤ አስታውቀዋል፡፡
“…ኃላፊነቶ የተነሳሎት መሆኑን አስታውቃለሁ” በሚል ነው በሚኒስትሩ የተጻፈው ደብዳቤ የሚነበበው፡፡
ፕሮፌሰሩ በምን ምክንያት ከኃላፊነታቸው ሊነሱ እንደቻሉ ግን በደብዳቤው የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
ደብዳቤውን በተመለከተም ሚኒስቴሩ በማህበራዊ ገጾቹም ሆነ በድረ-ገጽ አድራሻው የሰጠው ይፋዊ መግለጫም ሆነ ማስታወቂያ የለም፡፡
ሆኖም ፕሬዝዳንቱ ከሚኒስቴሩ የደረሳቸውንና የተሰጣቸው ኃላፊነት መነሳቱን የሚገልጸውን ደብዳቤ በስማቸው ባለ የትዊተር የማህበረሰብ ትስስር ገጽ ለጥፈዋል፡፡
ከደብዳቤው ጋር አያይዘው ባሰፈሩት ጽሁፍ ዩኒቨርስቲውንና ህዝባቸውን ማገልገል በመቻላቸው ያመሰገኑ ሲሆን የሃላፊነት ዘመናቸው ከተጠናቀቀ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን መቆየቱን እና ይህንንም ለሚመለከታቸው ባለስልጣናት ማስታወቃቸውን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም የተሰጣቸው ኃላፊነት የመነሳቱ ነገር በቅርቡ የተካሄደውን የትግራይ ክልል ምርጫ ለመታዘብ እንደመጡ አስታውቀው ከነበሩት ከኖርዌያዊው ጀትል ትሮንቮል ጋር “መገጣጠሙ አስገርሞኛል” ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የገጠሟቸው ችግሮች እንደነበሩ በተመሳሳይ በትዊተር ገጻቸው ያስታወቁት ትሮንቮል ዛሬ ጠዋት ወደ ኖርዌይ ተመልሰዋል፡፡
ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ለተለያዩ የምርምር ስራዎች ተመልሰው ወደ ዩኒቨርስቲው ዳግም ይመጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸው ነው ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት የገለጹት፡፡