”ሕወሓት በኦሮሞ ህዝብና ታጋዮች ላይ ላደረሰው ጉዳት ይቅርታ ካልጠየቀ ከፓርቲው ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም”-ኦነግ
ራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት” ብሎ የሚጠራውን የትጥቅ ትግል የሚያደርግ ድርጅት ኦነግ አውግዟል
ኦነግ “አቶ ዳውድ ኢብሳ ከፓርቲው መመሪያ ውጭ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው” መታገዳቸውን ገለጸ
”ሕወሓት በኦሮሞ ህዝብና ታጋዮች ላይ ላደረሰው ጉዳት ይቅርታ ካልጠየቀ ከፓርቲው ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም”-ኦነግ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ ድርጅቱን ለ21 ዓመት የመሩትን አቶ ዳውድ ኢብሳን ከሊቀመንበርነት ማንሳቱን አስታወቀ፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ቀጄላ መርዳሳ አቶ ዳዉድ ኢብሳ በሊቀመንበርነት በቆዩባቸው 21 ዓመታት “የድርጅቱን ገንዘብና ሀብት ብቻቸውን ሲያዙበት ኖረዋል ፤ በድርጅቱ ውስጥ አድልዎ በመፍጠር የአካባቢያቸውን ሰዎችና ዘመዶች ቁልፍ የስራ መደቦች ላይ በመመደብ ጥቅማቸውን አስጠብቀዋል” ሲሉ ለአል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል ። ግንባሩ የሊቀመንበሩን መታገድ በተመለከተ መግለጫም አውጥቷል፡፡
መግለጫው አቶ ዳውድን “በዚህ መሰል ኣካሄድ ከድርጅቱ ህገ ደንብና አሰራር ውጭ የራሳቸውን አምባገነንነት በድርጅቱ ላይ አነግሰዋለ” ያለ ሲሆን “አቶ ዳዉድ ኢብሳ 21 ዓመት በሊቀ መንበርነት በቆዩበት ጊዜ ድርጅቱ ፈራርሶ ከነበረበት ወረደ እንጂ እድገት አላሳየም” ብሏል። አቶ ዳውድ በአመራር ዘመናቸው የኦነግ ዋና አመራርና መዋቅሩ እንዲፈርስ ማድረጋቸውንና የጋራ አመራር የሚለው በሃሳብ እንጂ በተግባር ሊታይ እንዳልቻለ ፓርቲያቸው ገልጿል፡፡
አሁን ላይ ኦነግ ዉስጥ የተማሩና ልምድ የቀሰሙ አባላት ቁጥር አነስተኛ መሆኑን የገለጸው ግንባሩ ለዚህ ደግሞ “ተጠያቂው አቶ ዳዉድ ናቸው” ብሏል፡፡
ግንባሩ ብዙ አመታት ባስቆጠረው የኦሮሞ ነጻነት ትግል ውስጥ ኦነግ ከተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦች ትግል ጋር የትግል አጋርነትና ወዳጅነት ለመፍጠር ጥረቶችእንዳደረገ ያነሳ ሲሆን ይህም የትግል አጋርነትና ወዳጅነት በእኩልነት፣ በመከባበርና በዲሞክራስያዊ መርህ ላይ መሆንን መሰረት ያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡
ለታክቲክ ወይም ለግዜያዊ ጥቅም ተብሎ የሚደረግ ትብብር ዘለቄታዊ ጥቅም እንደማያስገኝ ያነሳው የግንባሩ መግለጫ በተለይም ሕወሓት በኦሮሞ ህዝብና በኦሮሞ ታጋዮች ላይ ላደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ይቅርታ ጠይቆ በኦሮሞ ህዝብ ቅቡልነት አስኪያገኝ ድረስ ኦነግ ከዚህ ድርጅት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ይሁንና አቶ ዳዉድ ኢብሳ ከአመራሩ ዕውቅና ውጪ የፋይናንስ ሰራተኛቸውን በቅርቡ መቀሌ በተካሄደው የህወሃት ስብሰባ ላይ አንዲሳተፍና ግንኙነት እንዲያደርግ መላኩ የግንባሩን ፖሊሲ የጣሰ ህገ ወጥ ድርጊት መሆኑን ነው ፓርቲው የገለጸው። ኦነግ በኦሮሞና በትግራይ ህዝብ መካከል ያለው ወንድማዊና ዘላቂ ግንኙነት አንዲጠናከር እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡
ኦነግ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግና ያለውን ድክመት ለማረም እንደሚሰራ የገለጸው መግለጫው ፣ “አቶ ዳውድ ኢብሳ ከድርጅቱና ከሀገሪቱ የፓርቲ ህግና ደንብ ውጪ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የአቶ ዳውድን ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን አንዲከታተል” ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡
በመሆኑም “አቶ ዳውድ የኦነግ ሊቀ መንበር የሚል ስም በመጠቀም ከቦርዱና ከተለያዩ አካላት ጋር ግንኙነት ለማድረግ የሚያደርጓቸው ጥረቶች በድርጅቱ ተቀባይነት የላቸውም” ይላል መግለጫው፡፡ ግንባሩ ጠቅላላ ጉባዔ አድርጎ አዲስ መሪ እስኪመረጥ ድረስ ምክትል ሊቀ መንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ የድርጅቱ ተወካይና መሪ እንዲሆኑ መወሰኑ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል፡፡
“ከኦነግ ከፍተኛ አመራር ውስጥ ሊቀ መንበሩ ያሰማሯቸው ጥቂት ግለሰቦች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን መቀላቀላቸውና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰራዊት ከፍተኛ አመራር በማለት በትጥቅ ትግል ለመቀጠል መርጠዋል” ያለው የኦነግ መግለጫ “ጥቂት አባላት በስልክ ሰራዊቱን ለመገናኘት መሞከርና የሰላማዊ ትግሉን ስነ ምግባር ያለማክበር ድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል” ሲል ገልጿል፡፡
ይህም በተለይም በወለጋና ጉጂ የሚኖረው ህዝብ ላይ ከፍተኛ ወከባ፣ የሀገር ውስጥ ስደት፣ የህይወትና የንብረት ጉዳት በማስከተል የህዝቡን የመንቀሳቀስ ነጻነትና ሰላማዊ ኑሮ ማናጋቱን አስታውቋል፡፡
በውጭ ያሉ ጥቂት የድርጅቱ አመራር አባላት የነበሩ ግለሰቦችም “ከትጥቅ ትግል ውጪ የሚያዋጣን የለም” በማለት ገንዘብ በማሰባሰብና በየጊዜው በማህበራዊ ሚዲያና በኦኤንኤን (ONN) ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ወጥተው በኦነግ ስም የሚያስተላልፉት መልዕክትና የሚያደርጉት ቅስቀሳዎችና ጥሪዎች ከድርጅቱ የትግል ስትራቴጂና ከሀገሪቷ ህግ ጋር የሚጣረሱ በመሆናቸው” በድርጅቱ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንዳሳደረ በመግለጫው አካቷል፡፡
“ከፊል የድርጅቱን የአመራር አባላት የትጥቅ ትግል ደጋፊዎች፣ ሌሎችን ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሚፈልጉና ከመንግስት ጋር ያበሩ በማለት የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄዱ ራሳቸውን ወደር የማይገኝለት የነጻነት ታጋይ አስመስለው በማቅረብ በድርጅቱ ውስጥ መከፋፈል አንዲኖር በሰፊው ዘመቻ አካሂደዋል” ብሏል ግንባሩ ባወጣው መግለጫ፡፡
ከዚህ ቀደም አቶ ዳውድ በጊዜያዊነት ስለመታገዳቸው አል ዐይን አማርኛ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ አሁን ድርጅቱ ስላሳለፈባቸው ዉሳኔ እንዲሁም በተያያዥነት ስላወጣው መግለጫ አቶ ዳውድ ኢብሳን ለማናገር በእጅ ስልካቸው ላይ ለመደወል ብንሞክርም ስልካቸው ባለመስራቱ አል ዐይን ሀሳባቸውን ማካተት አልቻለም፡፡