ታወር 22 በጆርዳን ውስጥ ስትራቴጂካዊ በሆነው በሶሪያ እና ኢራቅ ድንበር አቅራቢያ ይገኛል
የአሜሪካ ወታደሮች ስለተገደሉበት 'ታወር 22' የሚታወቁ እውነታዎች ምንድናቸው?
በጆርዳን የሚገኘው 'ታወር 22' የተባለው የጦር ሰፈር በድሮን ተመቶ ሶስት የአሜሪካ ወታደሮች በትናንትናው እለት ተገድለዋል።
- በዮርዳኖስ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት 3 የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ ከ34 በላይ ቆሰሉ
- የወታደሮቹን ግድያ ተከትሎ ባይደን ኢራንን በቀጥታ እንዲደበድቡ ጫና እየተደረገባቸው ነው
ሮይተርስ ስለታወር 22 የሚከተለውን ዘግቧል።
የሚገኝበት ቦታ
ታወር 22 በጆርዳን ውስጥ ስትራቴጂካዊ በሆነው በሶሪያ እና ኢራቅ ድንበር አቅራቢያ ይገኛል።
አላማው
ስለጦር ሰፈሩ ብዙ መረጃዎች የለም። ነገርግን ቦታው ጥቂት ቁጥር ያላቸው የአሜሪካ ወታደሮች ያሉበት በአል ታንፍ ካምፕ አቅራቢያ በሶሪያ ድንበር ይገኛል።
የታንፍ ካምፕ አይኤስን ለመዋጋት ወሳኝ ሚና እንደነበረው ይገለጿል። አሜሪካ ታንፍን ኢራን በምስራቅ ሶሪያ የምታደርገውን ወደታደራዊ ግንባታ ለመከላከል ትጠቀምበታለች የሚልም ግምትም አለ።
ጥቃት የደረሰበት ታወር22 በታንፍ ሰፍረው ለሚገኙት የአሜሪካ ወታደሮች ቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ነው።
የአሜሪካ ወታደሮች በጆርዳን
የጆርዳን ጦር ከፍተኛ የአሜሪካን ፋይናንስ ከሚቀበሉት አንዱ ነው።
ጆርዳን ብዙ ወታደሮቿ በአሜሪካ የሰለጠኑ ሲሆን አሜሪካ አመቱን መሉ ወታደራዊ ልምምድ ከምታደርግባቸው የመካከለኛው ምስራቅ አጋሮቿ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች።
የሶሪያ ጦርነት በፈረንጆፈቹ 2011 ከተጀመረ ወዲህ አሜሪካ አማን የድንበር ደህንነት ስርአት እንዲኖራት በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን አውጥታለች።
ጥያቄ የሚፈጥሩ ጉዳዮች
በታወር 22 ምን ያህል የአሜሪካ ወታደሮች ሰፍረው እንደነበር አልታወቀም። ከዚህ በተጨማሪም በቦታው ምን አይነት የጦር መሳሪያ፣ የአየር መከላከያ ስርአት ጥቅም ላይ እንደዋለ እና በትክክል ምን እንደተፈጠረ ግለጽ አይደለም።
አሜሪካ ጥቃቱን ያደረሱት በኢራን የሚደገፉ ታጣቂዎች ናቸው ብላለች።
ፕሬዝደንት ባይደን አሜሪካ ለጥቃቱ ምላሽ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።
ኢራን በዚህ ጥቃት እጄ የለበትም ስትል የሚቀርብባትን ክስ አስተባብላለች።
የወታደሮቹን ግድያ ተከትሎ የአሜሪካ ሪፐብሊካኖች ፕሬዝደንት ባይደን ወታደሮቹን ለጥቃት አጋልጠዋቸዋል የሚል ክስ አቅርበዋል። ሪፐብሊከኖቹ ባይደን በኢራን ላይ ቀጥተኛ ጥቃት እንዲሰነዝሩም ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።