በይፋ ያልተሾመው የሶሪያ መሪ አህመድ አል ሻራ የውጭ ዲፕሎማቶችን በማስተናገድ በንቃት እየተሳተፈ ነው
አዲሶቹ የሶሪያ መሪዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ሾመዋል።
በሽር አላሳድ ከልጣን ከተወገደ ከሁለት ሳምንታት በኋላ አለም አቀፍ ግንኙነት ለመገንባት እየሞከሩ ያሉት አዲሶቹ የሶሪያ መሪዎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሾማቸውን ሮይተርስ የሶሪያን ዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
ሀገሪቱን እየመራ ያለው ጠቅላይ እዝ አሳድ ሀሰን አል ሺባኒን ውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ማድረጉን ዘገባው ጠቅሷል።
በአዲሱ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ምንጮች ለሮይተርስ እንደተናገሩት ሹመቱ የተሰጠው ሶሪያውን ሰላም እና መረጋጋት የሚያመጣ አለምአቀፍ ግንኙነት እንዲመሰረት ያላቸውን ጽኑ ፍላት እውን እንዲሆን ለማድረግ ነው።
አል ሽባኒ ማን እንደሆኑ የሚገልጽ ዝርዝር መረጃ አልወጣም።
በይፋ ያልተሾመው የአሁኑ የሶሪያ መሪ አህመድ አል ሻራ የተመድ የሶሪያ ልኡክን እና ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ጨምሮ የውጭ እንግዶችን በማስተናገድ በንቃት እየተሳተፈ ነው።
ዋና ትኩረቴ የሶሪያ መልሶ ግንባታ ነው ያለው ሻራ ከአለምአቀፍ ልኡካን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማድረግ እንደሚፈልግ አመላክቷል። ለአዲስ ጦርነት ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል ሻራ።
አሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) የአሳድን አስተዳደር በመገርሰሱ ደስተኛ ቢሆኑም ቡድኑ ጥብቅ እስላማዊን ህግ ይመሰርታል ወይስ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ይከተላል የሚለው ግልጽ አይደለም።
በ 2016 ሻራ ግንኙነት ከማቋረጡ በፊት ኤችቲኤስ የአልቃ ኢዳ አካል ነበር።
በአህመድ አል ሻራ ወይም አል ጆላኒ የሚመሩት የሶሪያ ታጣቂ ቡድኖች ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ በፈጸሙት ጥቃት ደማስቆን መቆጣጠራቸው የአሳድ ቤተሰባዊ አስተዳደር እንዲገረሰስ እና አሳድም ሀገር ጥሎ እንዲሰደድ አድርገዋል።
የአሳድ አስተዳደርን እንዲያስወግድ እና እስላማዊ የሸርዓ ህግ እንዲያቋቁም ኢራን ተልኮ ሰጥታዋለች በሚል አሜሪካ ሻራን በ 2013 በሽብር ፈርጃዋለች።
የአሜሪካ ባለስልጣናት በደማስቆ ተገኝተው ከሻራ ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ እንደተናገሩት ዋሽንግተን ሻራ ያለበትን ለጠቆመ 10 ሚሊዮን ዶላር እሸልማለሁ የሚለውን ጥሪ መሰረዟን በትናንትናው አስታውቀዋል።