ሩሲያ፤ “ዓላማዬን እስከማሳካ የሚቆም ወታደራዊ ዘመቻ የለም” አለች
የዩክሬን ጦር በመልሶ ማጠቃት እርምጃ ለሩሲያ ኃይሎች ወሳኝ የአቅርቦት ማዕከል የሆነችውን “ኩፒያንስክ” ተቆጣጥሯል
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ፤ በሞስኮ እና በኪቭ መካከል የሚደረጉ "የድርድር ተስፋዎች የሉም" ብለዋል
በዩክሬን ጦር መልሶ ማጥቃት ከቁልፍ ወታደራዊ ይዘታዎች ያፈገፈገችው ሩሲያ “ዓላማዬን እስከማሳክ የሚቆም ወታደራዊ ዘመቻ የለም” አለች።
ሞስኮ ይህን ያለችው ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ኃይሎች በወሰዱት የመልሶ ማጥቃት እርመጃ የሩሲያ ኃይሎች ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለመልቀቅ መገደዳቸውን ተከትሎ “ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ዘመቻ ታቆም ይሆን?” በሚል ለሚነሳው ጥያቄ በሰጠችው ምላሽ ነው።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "ልዩ ወታደራዊ ዘመቻው መጀመሪያ ላይ የተቀመጡት አላማዎች እስኪሳኩ ድረስ ይቀጥላል" ብለዋል።
አሁን ላይ የሩሲያ አየር፣ ሮኬቶችና መድፍ ኃይሎች የኩፒያንስክ እና ኢዚዩም የከተማ ማዕከሎችን ጨምሮ በዩክሬን የጦር ኃይሎች ይዞታወች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በመሰንዘር ላይ እንደሆኑም ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ ከኪቭ ጋር ሊኖሩ ስለሚችሉ የሰላም ንግግሮች ተጠይቀውም፤ በሞስኮ እና በኪቭ መካከል የሚደረጉ "የድርድር ተስፋዎች የሉም" የሚል ምላሽ መስጠታቸው ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ኃይሎች የወሰዱት እርምጃን ተከትሎ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ካርኪቭ ግዛት ውስጥ ከሚገኙት ሁለት አካባቢዎች (ባላክሊያ እና ኢዚየም ) ለማፈግፈግ መገደዳቸው ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህም የዩክሬን ባለስልጣነት ወታደሮቻቸው ለሩሲያ ኃይሎች ወሳኝ አቅርቦት ማዕከል የሆነችውን ኩፒያንስክ መቆጣጠራቸው በመግለጽ ላይ ናቸው።
ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ቅዳሜ በሰጡት መገለጫ፤ወታደሮቻቸው በወሰዱት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ “2 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ከሩሲያ ነጻ መውጣቱ” ተናግረዋል።
የጦር ግስጋሴው ሩሲያ በሚያዝያ ወር በኪቭ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎች ከወጣች በኋላ የተገኘ በጣም ጠቃሚ ስኬት ነው ተብሎለታል።
የዩክሬን ባለስልጣነት ይህን ይበሉ እንጂ ፤ የሩሲያ ወታደሮች ያፈገፈጉት የዩክሬን መሪዎች እንደሚሉት ሳይሂን ለዓላማ እንደሆነ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሼንኮቭ ተናግረዋል።
ወታደሮቹ ከባላክሊያ እና ኢዚየም አካባቢዎች አፍግፍገው በዶኔትስክ ክልል ተሰባስበዋል ያሉት ኢጎር ኮናሼንኮቭ ፤ የተወሰደው የማፈግፈግ እርምጃ በምስራቅ ዩክሬን የመትገኘውን ዶንባስ ግዛት ነጻ ለማውጣት የሚያስችል በቂ ዝግጅት ለማድረግ ያለመ መሆኑ ገልጸዋል።