ሩሲያ፤ በቁጥጥሯ ስር ባሉ የዩክሬን ግዛቶች በመጪው ህዳር ወር “ህዝበ ውሳኔ” ልታካሂድ ነው
የሩሲያ ገዥ ፓርቲው ዋና ጸሃፊ፤ ህዝብ ውሳኔ ማካሄድ "ትክክል እና ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው" ብለዋል
ህዝብ ውሳኔው “በድንበሮች የተከፋፈለውን የሩሲያ የተሟላ የግዛት አንድነት የሚመልስ ነው” ተብሏል
የሩሲያ ገዥ ፓርቲ በሩረሲያ ጦር ስር በሚገኙ ግዛቶች የፊታችን ህዳር 4 ቀን 2022 ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ማቀዱ አስታወቀ።
የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አንድሬ ቱርቻክ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው እንዳስታወቁት ህዝብ ውሳኔው በህዳር ወር ማካሄድ "ትክክል እና ምሳሌ ሊሆን የሚችል ነው" ብለዋል።
ዋና ጸሃፊው ከህዝበ ውሳኔው በኋላ "ዶኔትስክ, ሉሃንስክ እና ሌሎች በርካታ የሩሲያ ከተሞች በመጨረሻ ወደ ሀገራቸው ወደብ ይመለሳሉ፤ በዚህም አሁን በመደበኛ ድንበሮች የተከፋፈለው የሩሲያ የተሟላ የግዛት አንድነት አውን ይሆናል” ሲሉም ተናግረዋል።
ሩሲያ ፤ በቁጥጥሯ ስር ባለችው የዩክሬን ኬርሰን ግዛት ሰሞኑን ለማካሄድ አቅዳ የነበረውን “ህዝበ ውሳኔ ለጊዜው ማዘግየቷን” ኪሪል ስትሬሞሶቭ የተባሉና የሩሲያ ደጋፊ የሆኑ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ከቀናት በፊት መናገራቸው ሚታወስ ነው።
ኪሪል ስትሬሞሶቭ የአሁኑን ሩሲያ ውሳኔ ተከትሎ እንዳሉት፤ በዩክሬኗ ኬርሰን ግዛት የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ በህዳር ወር ለማካሄድ ዝግጁ መሆናቸው ተናግረዋል።
ስትሬሞሶቭ "ምንም እንኳን ይህ ህዝበ ውሳኔ አሁን እንዲካሄድ ዝግጁ ብንሆንም፣ ለዚህ ትክክለኛ ቀን እንዘጋጃለን " ማለታቸውም ሮይተርስ ዘግቧል።
የክሬምሊን ባለስልጣናት፤ የሩሲያ ጦር የተቆጣጠራቸው የዩክሬን ግዛቶች በተለይም በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙት አካባቢዎችን ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ህዝበ ውሳኔ ሊያካሂዱ መሆኑ ከሁለት ወራት በፊት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
የዩክሬን ግዛቶች የሆኑት ሉሃንስክ እና ዶንባስ ግዛቶች በሩሲያ፣ ሶሪያ እና ሰሜን ኮሪያ የሉዓላዊ ሀገርነት እውቅና ማግኘታቸውም አይዘነጋም።
ያም ሆኖ ዩክሬን እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ድርጊቱን ኮንነዋል።
የሩሲው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬናውያን የሩሲያን ዜግነት ሊያገኙ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያቀል አዲስ አዋጅ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
እርምጃውን የተቃወሙ የኪቭ ባለስልጣናት አዋጁ ህጋዊነት እንደሌለውና ተቀባይነት እንደማያገኝ ሲገልጹ ተስተውለዋል።