ፕሬዝደንት ዘሌሰንኪ ወታደሮቻቸው በወሰዱት የማጥቃት እርምጃ 2 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ከሩሲያ ነጻ መውጣቱን ተናገሩ
በዩክሬን ኃይሎች የመልሶ ማጥቃት እርመጃ የሩሲያ ኃይሎች ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለመልቀቅ ተገደዋል
የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሼንኮቭ፤ ወታደሮቹ ያፈገፈጉት "እንደገና ለመሰባሰብ” ነው ብለዋል
በዩክሬን ኃይሎች የመልሶ ማጥቃት እርመጃ የሩሲያ ኃይሎች ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ለመልቀቅ መገደዳቸው ተገለጸ፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር፤ ባለፈው ሳምንት የዩክሬን ኃይሎች የወሰዱት እርምጃን ተከትሎ የሩሲያ ጦር በዩክሬን ካርኪቭ ግዛት ውስጥ ከሚገኙት ሁለት አካባቢዎች ለማፈግፈግ ተገዷል ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሼንኮቭ፤ ወታደሮቹ ከባላክሊያ እና ኢዚየም አካባቢዎች ወደ ዶኔትስክ ክልል መሰብሰቡም ተናግረዋል ።
ኮናሼንኮቭ እርምጃው እየተካሄደ ያለው ሩሲያ ሉዓላዊ መሆኗ እውቅና የሰጠቻትን በምስራቅ ዩክሬን የመትገኘውን ዶንባስ ግዛት ነጻ ለማድረግ ያለመውን ወታደራዊ ዘመቻ ለማሳካት ነው ቢሉም፤ የዩክሬን ባለስልጣናት ግን ትልቅ ድል እየተቀዳጁ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ባለስልጣናቱ ወታደሮቻቸው ለሩሲያ ኃይሎች ወሳኝ አቅርቦት ማዕከል የሆነችውን ኩፒያንስክ መቆጣጠራቸው ገልጸዋል፡፡
የጦር ግስጋሴው ሩሲያ በሚያዝያ ወር በኪቭ ዙሪያ ካሉ አካባቢዎች ከወጣች በኋላ የተገኘ በጣም ጠቃሚ ስኬት ነው ተብሎለታል፡፡
ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ትናንት ማምሻውን በሰጡት መገለጫ፤ወታደሮቻቸው በወሰዱት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ “2 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር ቦታ ከሩሲያ ነጻ መውጣቱ” ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ውስጥ ግማሽ የሚሆነው ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ እንደገና እንደተያዘ መግለጻቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዩክሬን ኃይሎች የመልሶ ማጥቃት እርምጃና ግስጋሴ፤ የዩክሬን ጦር በሩሲያ ኃሎች ቁጥጥር ስር ግዛቶችን መልሶ የመውሰድ አቅም እንዳለው የሚያሳይ እንደሆነ ተደርጎ ተወስዷል።
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ፤ እየተገኙ ያሉ ድሎች የዩክሬን ኃሎች የሩሲያ ጦርን ማሸነፍ እንደሚችሉ አማላካች ናቸው ብለዋል፡፡
ጦርነቱ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ምዕራባውያንና የዩክሬን አጋሮች የሚያደርጉት የጦር መሳሪያ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉበት ሲሉም ተማጽነዋል፡፡