ሩሲያ የአውሮፓ ሀገራት በዩክሬን የሰላም አስከባሪ ጦር ለማሰማራት ማቀዳቸውን አጥብቃ ተቃወመች
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር 30 ሺህ ወታደሮችን በዩክሬን ለማሰማራት የያዙትን እቅድ ለትራምፕ ለማቅረብ አስበዋል

ክሪምሊን ባወጣው መግለጫ በሩስያ ድንበር ላይ የሚደረግ የማንኛውም የኔቶ አባል ሀገር ወታደራዊ እንቅስቃሴ አልቀበልም ብሏል
በሰላም አስከባሪ ስም የአውሮፓ ወታደሮችን ወደ ዩክሬን የመላክ ማንኛውም እቅድ ተቀባይነት እንደሌለው ክሪምሊን አስታወቀ፡፡
የክሪምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በዛሬው ዕለት በሰጡት መግለጫ ሀገራቸው ጉዳዩ እንደሚያሳስባት እና በቅርበት እየተከታተለችው እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በሞስኮ እና በኪየቭ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ሲደረግ እንደ የደህንነት ዋስትና የብሪታንያ ወታደሮችን በዩክሬን መሬት ላይ ለማስፈር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
ስታርመር 30 ሺ የአውሮፓ ሀገራት ወታደሮች በዩክሬን የሚሰማሩበትን እቅድ እና አሜሪካ ለዚህ እቅድ ድጋፍ እንድታደርግ ለመጠየቅ ከትራምፕ ጋር በቅርቡ እንደሚነጋገሩ ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞ በዩክሬን እና በአውሮፓ የደህንነት ዋስትና ዙሪያ በፓሪስ በተደረገው አስቸኳይ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሀገራቱ የሰላም አስከባሪ ወታደር እንዲያዋጡ ጥያቄ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር የጠበቁትን ያህል ይሁንታ አላገኙም፡፡
ጀርመን እና ፖላንድን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት በዩክሬን ምድር ወታደሮቻቸውን ለመላክ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ጉዳዩን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር “የቀረበው ሀሳብ ከኔቶ አባል ሀገራት የተውጣጡ ሃይሎችን ስለሚያካትት ለሩሲያ የደህንነት ችግር ምክንያት በመሆኑ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ በሩስያ ድንበርም ሆነ አቅራቢያ የሚያደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከሩስያ ደህንነት ስጋት ጋር በተያያዘ በቀላሉ እንደማይታይ ገልጸዋል፡፡
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው “ወታደሮቹ ምንም እንኳን በተለየ ሰንደቅ አላማ ቢንቀሳቀሱም ለሩስያ ሉአላዊነት ቀጥተኛ ስጋት ተደርገው የሚታዩ ናቸው” ብለዋል።
ባሳለፍነው ማክሰኞ በሳኡዲ አረብያ ሪያድ በአሜሪካ እና በሩስያ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል በተደረገው ውይይት ዩክሬን አንድ ቀን አባል እንደምትሆን ኔቶ በ2008 የገባውን ቃል እንዲሰርዝ ሞስኮ ጠይቃለች፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከፈረንሳይ ፣ ብሪታንያ ፣ ጣሊያን እና ጀርመን አቻዎቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት አውሮፓውያን በዩክሬን የሰላም ድርድር ላይ እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ መስጠታቸው ተሰምቷል፡፡