ትራምፕ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪን “አምባገነን” ሲሉ ለጠሩበት ንግግር ዩክሬን ምን ምላሽ ሰጠች?
ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን አቻቸውን “ከምርጫ ውጪ የሚመራ አምባገነን” ሲሉ ወርፈዋቸዋል

የዋሽንግተን እና ኬቭ የአደባባይ ፍጥጫ ከሰሞኑ ተባብሶ ቀጥሏል
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን ጦርነት እና ከሩስያ ጋር በተጀመረው የድርድር ሂደት ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የዩክሬኑን ፕሬዝዳንት በተለያዩ ሸንቋጭ ቃላቶች ወርፈዋል፡፡
ዘለንስኪ በሳኡዲው የአሜሪካ ሩስያ ውይይት ላይ ዩክሬን አልተሳተፈችም በሚል ላነሱት ቅሬታ ትራምፕ በሰጡት ምላሽ ዜለንስኪን “ያለምርጫ እየገዛ የሚገኝ አምባገንን” ብለዋቸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ዘለንስኪ በአፋጣኝ ምርጫ የማያከናወን ከሆነ የሚያስተዳደረው ሀገር አይኖረውም” ብለዋል፡፡
በጦርነቱ አጀማመር እና አሁን እየተጓዘ ለሚገኘበት መንገድ ዘለንስኪን ተጠያቂ ያደረጉት ትራምፕ ፕሬዝዳንቱ ጦርነቱ እዚህ ከመድረሱ በፊት ማስቆም የሚችሉበት እድል እንደነበራቸው አንስተዋል፡፡
ይህን ንግግር ተከትሎ በትላንትናው ዕለት ከዴይሊ ሜል ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ቮለድሚር ዘለንስኪ “ትራምፕ በሩስያ የተሳሳተ መረጃ ምህዋር ውስጥ እየኖሩ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
ከሰሞኑ የሁለቱ ሀገራት የአደባባይ ፍጥጫ ከፍ ብሎ እየታየ በሚገኝበት ወቅት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን አቻቸውን "አምባገነን" ሲሉ መፈረጃቸውን ተከትሎ ኬቭ ምላሽ ሰጥታለች፡፡
ቀድም ሲል የዘለንስኪን መንግስት የሚተቹ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የትራምፕን ንግግር የሚቃወም ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንድሬ ሲቢጋ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ዩክሬን "በአውሮፓ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ እጅግ አሰቃቂ ወታደራዊ ጥቃትን ተቋቁማለች" ሲሉ ጽፈዋል፡፡
“የዩክሬን ህዝብ እና ፕሬዝዳንቷ የሩስያን ጫና ተቋቁመው ይቀጥላሉ፤ ማንም እጅ እንድንሰጥ ሊያስገድደን አይችልም” ነው ያሉት፡፡
አሜሪካም ሆነች ሩስያ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪን በመጥፎ ቃል መግለጽ አይችሉም ያሉት የዩክሬን አራተኛዋ ትልቅ ከተማ የዲኔፔር ከንቲባ ቦሪስ ፊላቶቭ በበኩላቸው፥ "ዘለንስኪን ልንወደው ወይም ልንጠላው እንችላለን፤ ድርጊቱን ልናወግዝ ወይም ልናደንቅ የምንችለው ዩክሬናውያን ብቻ ነን ምክንያቱም እሱ የኛ ፕሬዝደንት ነው” ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ የአምስት ዓመት ፕሬዚዳንታዊ የስልጣን ዘመን በግንቦት 2024 ያበቃ ቢሆንም ሀገሪቱ እየተመራችበት በምትገኝበት ወታደራዊ አስተዳር (ማርሻል ሎው) ምክንያት አዲስ ምርጫ ሳይደረግ ጊዜው አልፏል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዘለንስኪ የአስተዳደር ጊዜ በማለቁ እንደ ህጋዊ የሀገር መሪ እንደማይቆጥሯቸው ደጋግመው ተናግረዋል ።
ትራምፕ ባሳለፍነው ማክሰኞ ባደረጉት ንግግር ደግሞ የፕሬዝዳንቱ ህዝባዊ ቅቡልነት ደረጃ በ4 በመቶ ላይ እንደሚገኝ እና አፋጣኝ ምርጫ እንዲደረግ መምከራቸው የሚታወስ ነው፡፡