የኩዌት መንግስት መልቀቂያ ያስገባው በተቃዋሚዎች ብርቱ ትችቶች ከቀረበበት በኋላ ነው
የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር ኩዌት መንግስት ራሱን ከስልጣን በማግለል፣የስልጣን መልቀቂያ አስገቷል፡፡
ከስምንት ወራት በፊት የተመሰረተው የጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሳባህ አል ካሊድ መንግስት ለሀገሪቱ ገዢ መልቀቂያ ማስገባታቸውን ኩዌት ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን መልቀቂያ ያስገቡት በሀገሪቱ ያጋጠመውን የፖለቲካ ውጥረት ለማርገብ አስበው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ኢኮኖሚያዋን በነዳጅ ንግድ ላይ የመሰረተችው ኩዌት የነዳጅ ገበያ ዝቅ ማለት ለፖለቲካ አለመረጋጋቱ ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡
የሀገሪቱ ሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት የጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሳባህ አል ካሊድ መንግስት ለኮሮና ቫይረስ የሰጠው ትኩረት አናሳ ነው፣በቫይረሱ ምክንያት የተዳከመውን ኢኮኖሚ ለማሻሻል የሰጠው ትኩረት አናሳ ነው የሚሉ ትችቶችን አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚህ የምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ባለመስጠቱ መንግስታቸውን ለማፍረስ ወስነዋል የሚሉ ዘገባዎች በመውጣት ላይ ናቸው፡፡የኩዌት ገዢ ኢምር ሼክ ናዋፍ አል አህመድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ አል ሳባህ የቀረበላቸውን የመልቀቂያ ጥያቄ መቀበላችንም የዜና ወኪሉ ዘግቧል፡፡
4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ጠቅላላ ህዝብ ብዛት ያላት ኩዌት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ያህሉ የኩዌት ዜጋ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የውጭ ሀገራት ዜጎች ናቸው፡፡