የመከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል በርካታ አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ
የተለያዩ ሀገራት እና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ውጊያው እንዲቆም ቢጠይቁም መፍትሔ አልተገኘለትም
ሠራዊቱ ወደ ፊት እየገሰገሰ እንደሚገኝ ጄኔራሉ ገልጸዋል
የመከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል በርካታ አካባቢዎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ
የመከላከያ ሠራዊት ዳንሻን ፣ ባከርን እና ከሽራሮ አስከ ሽሬ ያሉ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ምክትል ኤታማዦር ሹም እና የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።
“የህውሓት ቡድን ካልተደመሰሰ ሀገር ሰላም አትሆንም” ያሉት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የመከላከያ ሠራዊቱን የግዳጅ እንቅስቃሴ አስመልክተው እንዳስታወቁት፣ የመከላከያ ሠራዊቱ ከላይ የተጠቀሱትን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ወደ ፊት እየገሠገሠ ይገኛል።
መከላከያ "በከሀዲ ቡድኑ እጅ ያሉ ከባድ መሳሪያዎች ሙሉ በሙሉ ማውደሙን" ገልጸው በየቦታው ሠራዊቱን የከበበውን ኃይል እያራገፈ መሆኑን ጠቁመዋል።
ጄኔራሉ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ "ትናንሽ ክፍሎችን ከቦ የነበረው ኃይልም በሠራዊታችን ታላቅ ጀግንነት ተደምስሰዋል" ብለዋል፡፡
ከፍ ያለ ቁጥር ያለው የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ምርኮኛ እየሆነ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰራዊቱ እያሳየ ያለው ድጋፍ ከፍ ያለ የሞራል ልእልና እንዳላበሰውም ነው የገለጹት፡፡
የመከላከያ ኃይሉ ሕዝብ እንዳይጎዳ ለማድረግ ጽንፈኛ ኃይሉን ከህዝብ ለይቶ ለመምታት በጥንቃቄ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ጄኔራል ብርሃኑ ተናግረዋል ሲል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል።
በሌላ በኩል የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ፣ በክልሉ ኃይል ላይ በሁሉም አቅጣጫ ጥቃት እንደተከፈተ ትናንት ገልጸዋል፡፡ አሁንም የክልሉ ኃይል የመመከት አቅም እንዳለው በመግለጽ በአየር ኃይል የሚፈጸመውን ጥቃትም እንደሚከላከሉ ተናግረዋል፡፡ ምንም እንኳን የፌዴራሉ መንግስት በክልሉ የሚገኙ ከባድ መሳሪያዎችን እና ራዳሮችን ማውደሙን ቢገልጽም የጦር አውሮፕላኖችን የመምታት አቅምም እንዳላቸው ነው አቶ ጌታቸው የተናገሩት፡፡
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታትን ጨምሮ ዓለማቀፍ እና ቀጣናዊ ድርጅቶች እንዲሁም የተለያዩ ሀገራት ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ቢጠይቁም ውጊያው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡