በካሊፎርኒያ ግዛት ከተቀሰቀሱት 4 የሰደድ እሳት አደጋዎች ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር የዋለው አንዱ ብቻ ነው
ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በሎስአንጀለስ እና አካባቢው የተከሰተው ሰደድ እሳት 160 ስኩየር ኪሎሜትር ሸፍኗል
በአከባቢው በሰአት 100 ኪሜትር በሚነፍሰው ሀይለኛ ንፋስ የሚታገዘው እሳት በቀጣይ ቀናቶች ሊጠናከር እንደሚችል ተሰግቷል
በካሊፎርኒያ ግዛት በሎስ አንጀለስ እና አካባቢው ከተቀሰቀሱት 4 የሰደድ እሳት አደጋዎች ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር የዋለው አንዱ ብቻ መሆኑ ተነገረ፡፡
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ትላንት እና ዛሬን ጨምሮ ከሰሞኑ በሰአት 100 ኪሎሜትር እየነፈሰ በሚገኝው ሀይለኛ ንፋስ ሊባባስ እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡
በደቡባዊ ካሊፎርኒያ በክፍተኛ ንፋስ እና በደረቅ አየር ሁኔታዎች ምክንያት እሳቱ ሊባባስ ወይም አዲስ ሰደድ እሳት ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ መነገሩን ተከትሎ የእሳት አደጋ ሰራተኞችን በአዲስ የሰው ሀይል እና መሳሪዎች ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
የሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ መከላከያ አዛዥ አንቶኒ ማሮን “የእሳት አደጋ ሰራተኞች ባለፈው ሳምንት አደጋው ከተከሰተበት ወቅት በኋላ በተሻለ ሁኔታ ተዘጋጅተዋል፤ ነገር ግን ጥረቱን ስኬታማ ለማድረግ በአካባቢው የንግድ አውሮፕላኖችን በረራ ላልተወሰነ ጊዜ መከልከል ሊያስፈልግ ይችላል” ብለዋል፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ ለሳምንት በቀጠለው አደጋ አራት ዋና ዋና የሰደድ እሳቶች ከ160 ስኩየር ኪሎሜትር በላይ ማውደማቸው (መሸፈናቸው) ተገልጿል፡፡
ከተከሰቱት አራት አደጋዎች የእሳት አደጋ ሰራተኞች ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር መዋል የቻሉት አንዱን ብቻ ሲሆን በሰሜናዊ ሎስ አንጀለስ የሚገኝው ደግሞ 97 በመቶ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
የካሊፎርኒያ የደን እና የእሳት ጥበቃ ተቋም ባወጣው መረጃ 96 ካሬ ኪሎ ሜትር ያቃጠለውን እና በሎስ አንጀለስ ምዕራባዊ ክፍል የሚገኘው የ”ፓሊሳዴስ” እሳትን መቆጣጠር የተቻለው በ14 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ሌላኛው ከባድ የእሳት ቃጠሎ ከከተማዋ በስተምስራቅ በሚገኘው የሳን ገብርኤል ተራሮች ግርጌ ላይ የሚገኘው የ”እቶን” እሳት ሲሆን ቃጠሎው 33 በመቶው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
የሰደድ እሳት አደጋዎቹ እስካሁን የ24 ሰዎችን ህይወት ሲነጥቁ ሌሎች አድራሻቸው የጠፉ ሰዎችን የማፈላለግ ስራ በነፍስ አድን ሰራተኞች እየተሰራ ይገኛል፡፡
ከ100 በላይ የሚሆኑ የደቡብ ካሊፎርኒያ ነዋሪዎች ደግሞ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሳምንት በቀጠለው አደጋ በደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸው የአደጋ ምላሽ እና መልሶ ግንባታ እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አካባቢው ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ለማገገም 10 ቢሊየን ዶላሮችን ይፈልጋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ኮንግረሱ ይህን እቅድ በመደገፍ ከጎናቸው እንደሚቆም ተስፋ እንደሚደርጉ ገልጸዋል፡፡