የሰራተኞች የገቢ ግብር እንዲቀንስ ለመጠየቅ ሊደረግ የነበረው ሰልፍ ተሰረዘ
የጸጥታ ኃይሎች ሰልፉን በመከልከላቸው ለሰራተኞች ደህንነት ሲባል መሰረዙን ኢሰማኮ ገልጿል
የመስቀል አደባባዩ ሰላማዊ ሰልፍ "ይህን ጥያቄ ይዛችሁ ሰልፍ መውጣት አትችሉም" በሚል ተከልክሏል
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) ሚያዚያ 23 2023 በዓለም አቀፉ የሰራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) ሊያደርገው የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ በጸጥታ ቢሮ ክልከላ መሰረዙን አስታወቀ፡፡
የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ የሰራተኛው ችግሮችና ብሶቶች ይስተጋቡበታል የተባለው የመስቀል አደባባይ ሰልፍ መሰረዙን ለአል ዐይን አረጋግጠዋል፡፡
አል ዐይን መንግስት የኑሮ ዉድነትን አገናዝቦ የገቢ ግብርን እንዲቀንስ ይጠየቅበታል ስለተባለው ሰልፍ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ሆኖም የአዲስ አበባው ሰልፍና ከአንድ መቶ ሽህ በላይ ሰራተኞች ይሳተፉበታል የተባለው ሰልፍ በአስራ አንደኛው ሰዓት በከተማዋ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ መከልከሉ ተነግሯል፡፡
ማክሰኞ ሚያዚያ 17 የከተማ አስተዳደሩን ስለ ሰልፉ ማሳወቃቸውንና ከሰላምና ጸጥታ ቢሮ ጋር ሲነጋገሩ መሰንበታቸውን የተናገሩት ካሳሁን ፎሎ፤ ካላንደር በዘጋው ቀን ድምጻችንን እንዳናሰማ ተከልክለናል ብለዋል፡፡
"ሰልፉን ለማድረግ ፈቃድ አያስፈልግም፡፡ እኛ ለራሳችን ደህንነታችንን እንዲጠብቁን አሳውቀናል፡፡ የአዲስ አበባ ጸጥታ ቢሮ ይህን ጥያቄ ይዛችሁ አደባባይ አትወጡም አለን፡፡ ህግ እናስከብረለን ስላሉ ሰራተኛው እንዳይጎዳ አስቀረነው" ብለዋል፡፡
ለሰራተኛው ደህንነት ሲባል ሰልፉን ለመሰረዝ መገደዳቸውን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቱ፤ "እየተራበ [ሰራተኛው] ሌላ እርምጃ ተወስዶበት አስቸጋሪ ነው ብለን ለመሰረዝ መርጠናል" ብለዋል፡፡
"ግብግቡን በማስቀረት የሰው ህይወትን ማዳንን" መምረጣቸውንም ፕሬዝዳንቱ አክለው ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሰላምና ጸጥታ ቢሮው መሪነት ከፖሊስ ጋር ስለ መረሀ-ግብሩ ሲነጋገሩ አዎንታዊ ምላሽ እንደነበር የተናገሩት ካሳሁን ፎሎ፤ ቅዳሜ ስለ ሰልፉ መልዕክትና ጥያቄ መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው ክልከላ የገጠማቸው፡፡
የጸጥታ ቢሮውን ለማሳመን ያደረጉት ሙከራም "ይህን ጥያቄ ይዛችሁ መውጣት አትችሉም" በሚል ምላሻቸው እንደጸና ለአል ዐይን አሳውቀዋል፡፡
ሰራተኛው የሰልፉን መከልከል አውቆ እንግልት እንዳይገጥመውም የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት አደራ ብለዋል፡፡
ከ800 ሺህ በላይ አባል ሰራተኞችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) በሜይ ዴይ በዓል መንግስት የገቢ ግብርን እንዲቀንስ፣ ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል እንዲወሰን፣ የኤጄንሲ ሰራተኞች 20/80 ክፍያ ገቢራዊ እንዲደረግ እንዲሁም የመደራጀት መብት እንዲከበር ሊጠይቅ ወጥኖ ነበር፡፡