የሰራተኛ ማህበራት “መንግስት የገቢ ግብር እንዲቀንስ የሚጠይቅ ሰልፍ በ5 ከተሞች ላደርግ ነው” አለ
የኢትዮጵያ ሰራተኞች በኑሮ ውድነት ምክንያት ችግር ላይ ወድቀዋል ተባለ
በዓለም አቀፉ የሰራተኞች ቀን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ሰራተኞች ለጥያቄያቸው ሰልፍ ሊወጡ ነው
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) ለመንግስት ጥያቄ ለማቅረብ በሰራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዱን አስታወቀ።
መንግስት የገቢ ግብርን እንዲቀንስ ይጠይቅበታል የተባለው ሰልፉ አዲስ አበባን ጨምሮ በአምስት ከተሞች ይደረጋል ተብሏል።
የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት ካሳሁን ፎሎ ለአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ሰራተኛው በኑሮ ውድነቱ መኖር ባለመቻሉ ለመንግስት ጥያቄውን ለማቅረብ መገደዳቸውን ተናግረዋል።
በተለይም እንደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያሉና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ሰራተኞች ከ800 እስከ አንድ ሽህ 200 ብር በወር እየተከፈላቸው መኖር እንዳልቻሉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ ባለው የኑሮ ውድነት ለሳምንት ህይወትን መግፋት ተዓምር ሆኗል።
"ደሞዝ ተከፋዩ ሰራተኛ መኖር አልቻለም፤ የኑሮ ውድነቱ በጣም ከፍ ብሏል፤ በዚህ ኑሮ ውድነት መንግስት ድጎማ ወይም ጭማሪ ሊሰጠን አይችልም፤ ቢያንስ ግን በዚህ ችግር ወቅት ከኛ ከሚሰበስበው የስራ ግብር ይቀንስልን፤ ተርበናል፤ የምንበላው አጣን ብለን ነው የምንጠይቀው" ብለዋል።
መንግስት የገቢ ግብርን እንዲቀንስ በዓለም አቀፉ የሰራተኞች ቀን በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ፣ ሀዋሳ፣ ጅማና ሌሎችም ከተሞች ሰራተኞች አደባባይ እንደሚወጡ ተነግሯል።
ሰራተኞች የገቢያቸውን እስከ 35 በመቶ መቀረጣቸው ሳያበቃ፤ ውሎ አበላቸውና የትራንሰፖር ክፍያቸው እንዲሁም ሻይ ሲጠጡ 15 በመቶ ግብር መክፈላቸው ወቅቱን የዋጀ አይደለም ብለዋል።
ከ600 ብር በታች ገቢ ያላቸው ሰራተኞች ብቻ ግብር እንዳይከፍሉ መደረጉ ወቅታዊ የኑሮ ሁኔታን ያገናዘበ ባለሞሆኑ ዳግም ሊጤን ይገባል ያሉት የኢሰማኮ ፕሬዝዳንት፤ ከ10 ዓመት በፊት የወጣ ህግ በመሆኑ ሰራተኞችን ለችግር እየዳረገ ነው ብለዋል።
“መንግስት ከካዝናው አውጥቶ ደሞዝ ይጨምር የሚል ጥያቄ የለንም” ሲሉ የገለጹት ካሳሁን ፎሎ፤ ሆኖም ግን የሰራተኛውን ኪስ እያራቆተ ያለው የስራ ግብር መቀነስ አለበት ብለዋል።
ይህን ጥያቄ ለመንግስት የሚያቀርቡና ከተለያዩ የሰራተኛ ማህበራት ይውጣጣሉ የተባሉ በመቶ ሽህዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች የፊታችን ሰኞ ድምጻቸውን ያሰማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በአዲስ አበባ ብቻ ከከተማዋና ከዙሪያዋ አካባቢዎች ከአንድ መቶ ሽህ በላይ ሰልፈኞች ወደ ጎዳናዎች እንደሚወጡ ፕሬዝዳንቱ ለአል አይን ተናግረዋል።
ከግብር ይቀነስልን ባሻገር ሰራተኞች በቀናቸው አደባባይ ሲወጡ፤ ዝቅተኛ የደሞዝ ወለል እንዲወሰን፣ የኤጄንሲ ሰራተኞች 20/80 ክፍያ ገቢራዊት እንዲሁም የመደራጀት መብትን እንደሚጠይቁ ካሳሁን ፎሎ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሰማኮ) በ1955 ዓ.ም. የተመሰረተ ከ800 ሽህ በላይ ሰራተኞችን በአባልነት የያዙ ሁለት ሽህ 200 ማህበራትን ያቀፈ እናት ማህበር ነው።