ሐይቁን በሚቀጥሉት ዓመታት ወደነበረበት መመለስ እንደሚቻል ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ይገልጻል
ኳስ ሜዳና የእርሻ ቦታ ሆኖ የነበረው የሀሮማያ ሐይቅ ውሃ መያዝ ጀምሯል
የሀሮማያ ሐይቅ በምስራቅ ኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ 525 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምስራቅ ሀረረጌ የሚገኝ ሲሆን በ1996 ዓ.ም ነበር የደረቀው፡፡ ከ 17 ዓመት በፊት የሀሮማያ ሐይቅ በአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ስለሐይቁ በሚያውቁ ሁሉ ትልቅ ስምና ዝና ነበረው፡፡
በ1996 ሐይቁ ደርቆ ሙሉ ለሙሉ የእርሻ ቦታ ሆኖ ነበር፡፡ አርቲስቶች ብዙ የዘፈኑለት የሀሮማያ ሐይቅ እንዲመለስ ምሁራን ረጅም ጊዜ የፈጀ ጥናትና ምርምር አድርገዋል ፤ በማድረግም ላይ ናቸው፡፡ በ2012 ዓ.ም መጨረሻና በ2013 መጀመሪያ ወራት የጣለው ከመጠን በላይ ዝናብ ግን ሐይቁን ዳግም እንዲመለስ አድርጎታል፡፡
ሐይቁ መድረቁን ተከትሎ የእርሻ ማሳ ሆኖ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ቀደም ብሎ ውሃው ይተኛበት ከነበረው ውስጥ ብዙው ቦታ በውሃ ተሸፍኗል፡፡
በሀሮማያ ከተማ ሐይቁ አካባቢ ተወልዶ ያደገው አቶ መሐመድ አብዱራህማን የ ”ኢንቫይሮንመንታል ሄልዝ” (የአካባቢ ደህንነት) ባለሙያ ነው፡፡ ሐይቁ ከመድረቁ በፊት የከተማዋና የአካባቢው ነዋሪዎች ልዩ ድምቀትና የገቢ ምንጭ እንደነበረ የሚገልጸው አቶ መሐመድ አሁን እያየው ባለው ነገር መገረሙንና መደሰቱን አንስቷል፡፡
አቶ መሐመድ ከአል ዐይን ጋር ባደረገው ቆይታ አሁን ሐይቁ መመለሱ ደስታን ቢፈጥርም ይህንን ውሃ ግን እንደነበረ ማስቀጠል ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ይገልጻል፡፡
“አሁን ግን በተፈጥሮ ሂደት አዲስ ክስተት አይተናል፤ ለዚህ ደግሞ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በየዳርቻው የተተከሉት ዛፎች ከዝናቡ ኃያልነት በተጨማሪ ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው” ብሏል አቶ መሐመድ። ይህም ሆኖ አሁንም ገና ከመሙላቱ በርካታ ቆሻሻ እየተጣለበት እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን ፣ ቀድመው የነበሩ የውሃ መፍሰሻ ቦዮች ሰዎች በቦታው ላይ በመስፈራቸው መደፈናቸውንም አንስቷል፡፡ በሌላ በኩል ውሃውን በፓንፕ አላግባብ ለጫት ማሳ ይወስዱት ነበርም ብሏል።
አቶ መሐመድ ከተማ አስተዳደሩ የቆሻሻ መጣያ ቦታ ማዘጋጀት፣ የውሃ መፍሰሻዎችን እንደ አዲስ መገንባት፣ ወጣቶችን በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በአግባቡ ማደራጀትና ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር በሙያተኛ የታገዘ ጥበቃ ሊያደርግለት እንደሚገባ ያነሳል፡፡
በመንግሥትም ሆነ በአካባቢው ነዋሪ ሐይቁ ጥበቃ ሲደረግለት እንዳልነበረ ተገልጿል፡፡ በዚህም የተነሳ በአካባቢው ያለው ውሃ ሙሉ ለሙሉ ደርቆ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ ለጫት በተቆፈሩ ጉድጓዶች ቀርተው ነበር። በዙሪያው የነበሩትም ካፍቴሪያዎች ለመዘጋት በቅተው በርካቶች ሥራ ፈት እንዲሆኑ አድርጓል ይላል አቶ መሐመድ።
የሀሮማያ ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶ/ር ኢብሳ ኢብራሂም ቀደም ባለው ጊዜ ዝናብ ከዘነበ በኋላ ውሃ ቢቋጥርም ቶሎ እንደሚጠፋ አንስተው የአሁኑ ግን መቆየቱን ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡ አካባቢው የመዝናኛ ሃይቅ እንደነበር ያነሱት ምክትል ከንቲባው አሁን ሃይቁ ውሃ ይዞ በመቆየቱ በአካባቢ ከፍተኛ ደስታ ተፈጥሯል ይላሉ፡፡
አካባቢውን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ዕቅድ መኖሩን የገለጹት ምክትል ከንቲባው አሁን ላይ ምንጮች ሳይቀር እየተመለሱ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ በቀጣይ ከተማውና የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የፌዴራል መንግስት በሐይቁ መመለስና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ጥናት እያጠኑ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ቆሻሻ ወደ ሐይቁ እንዳይገባ ራሱን የቻለ የቆሻሻ መጣያ መዘጋጀቱን ያስታወቁት ምክትል ከንቲባው በየሳምንቱ ዕሁድ የጽዳት ዘመቻ እንዲዘጋጅ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል ሐይቁ ሲደርቅ የአካባቢው አርሶ-አደሮች የእርሻ ቦታ አድርገውት የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ሐይቁ ውሃ በመያዙ ራሱን ማስከበሩን አንስተዋል፡፡ በቀጣይ የሐይቁ ቦታ እንዲከበር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዶ/ር ኢብሳ የሐይቁ ውሃ አሁን እስከ 5 ሜትር ጥልቀት እንዳለው አንስተው 4ኪሎ ሜትር የሚሆን ርዝመት እንደሚሸፍንም ነው የገለጹት፡፡
የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ሐይቅ በተመለከተ ጥናት የሚያካሂድ ቡድን ማቋቋሙን አስታውቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ልማት ዳይሬክተርና የማህበረሰብ ተሳትፎና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶ/ር አድማሱ ቦጋለ ዩኒቨርሲቲው ሐይቁ ወደነበረበት እንዲመለስ ላለፉት 10 ዓመታት በተፋሰሱ ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ፣ ችግኝ የመትከል ሥራ ሲሰራ እንደነበር አንስተዋል፡፡ ይህንኑ ሥራ በጀት በመመደብ ሲሰራ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡ ዘንድሮ ዝናቡ በስፋትና በመጠን በርከት ብሎ ሐይቁ እየተመለሰ ስለሆነ የተጀመረውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ይበልጥ ለማጠናከር ይረዳናል ብለዋል፡፡
“ሐይቁ በሚቀጥሉት ዓመታት ወደነበረበት እንደሚመለስ መናገር ይቻላል” የሚሉት ዶ/ር አድማሱ ይህ እንዲሆን በፕሮጄክት ተይዘው የነበሩ ሥራዎችን ዩኒቨርሲቲው ሲሰራ “የማይመለስ ነገር ለምን ትሰራላችሁ” ስንባል ነበርም ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዙሪያ የባለሙያዎች ቡድን ማቋቋሙን የገለጹት ዶ/ር አድማሱ “አምስት ባለሙያዎች በዚህ ስራ ላይ ተሰማርተዋል” ብለዋል፡፡ ሀይቁ ወደነበረበት እንዲመለስ ከክረምቱ ከፍተኛ ዝናብ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው ለ 10 ዓመታት ያህል ሲሰራው የቆየው የችግኝ ተከላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
ሐይቁ ውሃውን እንደያዘ እንዲቀጥል ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ችግኝ እያፈላ ለህብረተሰቡ እንደሚያከፋፍል የገለጹ ሲሆን በዚህ ዓመትም ከ 358 ሺ በላይ ችግኝ በማፍላት መከፋፈሉን አንስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ላቋቋመው የተፋሰስ ጽ/ቤት በየዓመቱ አምስት ሚሊዮን ብር እየተበጀተ እንደሆነም ዶ/ር አድማሱ አንስተዋል፡፡
የሀሮማያ ሐይቅ የባለቤትነት አደራው ለዩኒቨርሲቲው ሙሉ ለሙሉ ከተሰጠ ዩኒቨርሲቲው ሐይቁን እንደነበረ የማድረግ ሙሉ አቅምና ችሎታ እንዳለውም ነው ዶ/ር አድማሱ ያስታወቁት፡፡
የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ “ሪሶርስ ኢኮኖሚስት” እና የጥናት ቡድን አባል ፕ/ር ፍቃዱ በየነ ፣ ሐይቁ የመመለስ አዝማማሚያ አሳይቷል ማለት እንደሚቻል ተናግረል፡፡
በደርግ ጊዜ ይህ ሐይቅ ሊጠፋ ይችላል የሚል ትንበያ እንደነበር የገለጹት ተመራማሪው ሐይቁ ውሃውን እንደያዘ እንዴት ሊቀጥል ይችላል የሚለው ጉዳይ የሚታወቀው የተጀመረው ጥናት ሲጠናቀቅ መሆኑን ነው ያነሱት፡፡ አሁን ላይ የሐይቁ አጠቃላይ ሁኔታ ስፋቱና ጥልቀቱ በትክክል ተጠንቶ ሲጠናቀቅ የሚታወቅና የሚገልጽ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ ውሃውን አሁንም ለመስኖ መጠቀም የሚፈልጉ እንዳሉና በፊት ሞተር ፓምፕ የነበራቸው ሰዎች አሁንም እንደያዙ መሆናቸውን የገለጹት ፕ/ር ፍቃዱ ውይይት ተደርጎ መፍትሔ ይፈለጋል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ሲታረስ የነበረውና ኳስ መጫወቻ ሆኖ የቆየው ሐይቅ በድጋሚ አንሰራርቷል፡፡ የአካባቢ ሰዎች እየዋኙበት ፣ ትናንሽ ጀልባዎችም እየተንቀሳቀሱበት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡