በአንኮበር ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ነዋሪዎች አካባቢውን እንዲለቁ ወረዳው አሳስቧል
ነዋሪዎቹ በጊዜያዊነት ተነስተው ሌላ ቦታ እንዲሰፍሩ ቦታ ይመቻቻል ተብሏል
በአንኮበር ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት ከ32 በላይ አርሶአደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው ወረዳው አስታውቋል
በአንኮበር ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት ከ32 በላይ አርሶአደሮች ጉዳት እንደደረሰባቸው ወረዳው አስታውቋል
በአማራ ክልል ሰሜንሸዋ ዞን አንኮበር ወረዳ ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት በመድረሱ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ወረዳው አሳሰበ፡፡
የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት እንደገለጸው በአንኮበር ወረዳ ጎረጎ ዙሪያ ቀበሌ በደረሰው አደጋ ከ32 በላይ አርሶ አደሮች የእርሻ መሬት ተጎድቷል፡፡ በወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አስጨናቂ የተመራ ልዑክ የጉዳቱን መጠን ለማየት በቦታው መገኘቱን ተገልጿል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ለንብረታቸውም ብቻ ሳይሆን ለሕይወታቸውም እንደሚሰጉ ገልጸው ከዚህ የከፋ አሳዛኝ ክስተት ከመፈጠሩ በፊት መንግሥት ለጊዜው ልጆቻቸውና ከብቶቻቸው የሚርፉበት ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አስጨናቂ ችግሩ በወረዳው አቅም የሚፈታ እንዳልሆነ ገልጸው ተጨማሪ ጥናት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በጊዜያዊነት ከቦታው ተነስተው ወደ ሌላ አካባቢ እንዲሰፍሩ መንግስት ቦታ እንደሚመቻች የገለጹት አቶ አዲሱ ቦታው እስኪመቻች ግን ነዋሪዎቹ በአፋጣኝ አካባቢውን ለቀው አቅራቢያ ወደሚገኙ ከተሞች እንዲሄዱና ልጆቻቸውን ከጥፋት አንዲታደጉ ጠይቀዋል፡፡ ዘላቂው መፍትሄ ግን ከሌሎች አካላት ጋር መነጋገርና መፍታት ነው ብለዋል፡፡