በጋዛ የሚገኘው ግዙፉ የአል ሽፋ ሆስፒታል ስራ ማቆሙን የአለም ጤና ድርጅት በትናንትናው እለት አስታውቋል
ግዙፉ የጋዛ ሆስፒታል ስራ አቆመ።
እስራኤል እያካሄደች ያለው ከባድ ጥቃት በቀጠለበት ወቅት፣ በጋዛ የሚገኘው ግዙፉ የአል ሽፋ ሆስፒታል ስራ ማቆሙን የአለም ጤና ድርጅት በትናንትናው እለት አስታውቋል።
አል ሽፋን ጨምሮ በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙ ሆስፒታሎች በእስራኤል ኃይሎች ስለተከበቡ ተካሚዎች ወደ ውስጥ መግባት አለመቻላቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም የአል ሽፋ ሆስፒታል የሀይል አቅርቦት በመቋረጡ ምክንያት አዲስ የተወለዱ ሶስት ህጻናት መሞታቸውን እና የሟቾች ቁጥር ከዚህም ሊጨምር እንደሚችልም የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል።
እስራኤል በጥቅምት ወር ጥቃት የፈጸመባት ሀማስ በሆስፒታሎች አቅራቢያ የማዘዣ ጣቢያ አቋቁሟል በማለት የምትሰነዝረውን ጥቃት ምክንያታዊ እያደረገች ነው።
በአል ሽፋ ሆስፒታል ያሉ የጤና ባለሙያዎችን ማናገራቸውን የገለጹት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ በጋዛ ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ እና ያለማቋረጥ ተኩስ የሚሰማበት ነው ብለዋል።
ዶክተር ቴድሮስ የህመምተኞች ሞት መጨመሩን እና የአል ሽፋ ሆስፒታል ስራ ማቆሙን በኤክስ ገጻቸው ገልጸዋል።
ዶክተር ቴድሮስ የተመድ ከፍተኛ ባለስልጣናት ተኩስ እንዲቆም ያቀረቡትን ጥሪ ደግፈዋል።
ደህንነታቸው መጠበቅ ያለበት ሆስፒታሎች ወደሞት እና ተስፋ መቁረጥ ቦታዎች ሲቀየሩ አለም ዝም ብሎ ማየት የለበትም ሲሉ ዶክተር ቴድሮስ ተናግረዋል።
በሀማስ የታገቱባትን ለማስለቀቅ እና ሀማስን ከምድረ ገጹ ለማጥፋት ያቀደችው እስራኤል በጋዛ የጀመረችውን መጠነ ሰፊ ጥቃት አጠናክራ ቀጥላበታለች።
የሰብአዊ መብት ተቋማት እና በርካታ ሀገራት እስራኤል በጋዛ ተኩስ እንድታቆም በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ። ነገርግን እስራኤል እና አጋሯ አሜሪካ ተኩስ እንዲቆም ፍላጎት የላቸውም።
ተኩስ አቁም ማለት ለአሜሪካ ሀማስ መልሶ እንዲደራጅ እና ድጋሚ ጥቃት እንዲፈጽም ማድረግ ነው።