ለእርዳታ ወደ 911 የደውለው የላስቬጋስ ነዋሪ በቤቱ ውስጥ በፖሊስ ተገደለ
ቤቱ ውስጥ የዘለቀውን ሰርጎ ገብ ሲፋለም የነበረው የ43 አመት ጎልማሳ በስህተት በፖሊስ ጥይት ተገድሏል
የሟቹ ቤተሰቦች ግድያውን የፈጸመው ፖሊሲ እንዲታሰር ቢጠይቁም ጉዳዩ በወንጀል ክስ አይታይም ተብሏል
በአሜሪካ ላስቬጋስ ለእርዳታ ወደ 911 የአደጋ ጊዜ ጥሪ ያደረገው ግለሰብ በፖሊስ ጥይት ተመትቶ ህይወቱ አልፏል።
ዱርሀም የተባለው የ43 አመት የላስቬጋስ ነዋሪ በመኖርያ ቤቱ አቅራቢያ የተኩስ ድምጽ መስማቱን እና ሁለት ሰዎች ወደ ቤት ውስጥ ሰብረው ለመግባት ጥረት ለማድረግ እየሞከሩ መሆኑን ገልጾ ለፖሊስ ይደውላል፡፡
የአደጋ ጊዜ ጥሪውን ተከትሎ ወደ አካባቢው ያቀኑት ፖሊሶች የተሰባበሩ የመኪና መስኮቶችን በሟቹ መኖርያ ቤት ደጅ ላይ ያገኛሉ ወደ ቤቱ ሲጠጉም ከውስጥ የጩኸት ድምጽ ይሰማ ነበር፡፡
አሌክሳንደር ቡክማን የተባለው ግድያውን የፈጸመው ፖሊስ የደረት ከሜራ ላይ ከፊት ለፊት ከደረቱ በላይ እርቃኑን በሆነ ሰው ላይ ጥይት ሲተኩስ ታይቷል፡፡
ሟቹ ድርሀም አሌሀንድራ ከተባለች የፊት ጭምብል ካጠለቀች ሰርጎ ገብ እጅ ላይ ስለት ለማስጣል እየታገለ ባለበት ወቅት ነው በፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ ያለፈው፡፡
ጥይቱን በተኮሰው ፖሊስ የደረት ካሜራ ላይ የተቀረጸው ምስል በሟቹ ላይ አምስት ጥይቶችን ከተኮሰ በኋላ “እጃችሁን አንሱ” ሲል ታይቷል፡፡
የቤቱ ባለቤት በተተኮሰበት ጥይት ወዲያው ህይወቱ ሲያልፍ በኋላ የ31 አመት ሴት እንደሆነች የተረጋገጠው አሌሀንድራ የተባለችው ተጠርጣሪ ደግሞ ቆስላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላለች፡፡
የዱርሀም ቤተሰቦች “ፖሊስ ስለት በያዘው ሰው ላይ ጥይት ሳይተኩስ ቤተሰቡን ከጥቃት ለመከላከል እየጣረ በሚገኝ አባት ላይ ባደረሰው ጥፋት ፍትህ እንዲሰጠን እንፈልጋለን” ብለዋል፡፡
የላስቬጋስ ፖሊስ ተበቃ ማህበር ግድያውን የፈጸመው አሌክሳንደር ቡክማን የተባለው ፖሊስ ሆነ ብሎ ጥቃት ለማድረስ አስቦ የፈጸመው ባለመሆኑ በወንጀል ክስ የመታየት እድሉ ጠባብ ነው ብሏል፡፡
የዱርሀም ሞት አሳዛኝ ቢሆንም ቡክ ማን ስራውን እየሰራ ነበር ወንጀል ለመፈጸም አላሰበም ብሏል ይህን ተከትሎም ጉዳዮ በፍትሀብሔር ችሎት የሚታይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ተጠርጣሪዋ ለዝርፍያ ወይም ሌላ ጥቃት ለመፈጸም ወደ መኖርያ ቤቱ ስለማቅናቷ እስካሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም ፖሊስ ከሟቹ ጋር የቀደመ የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸው ደርሸበታለሁ ብሏል::