ባለፉት 7 አመታት 3 ልጆችን ወልዳ የጣለችው እናት በፖሊስ እየተፈለገች ነው
ከ2017-2024 በህዝብ መናፈሻ ውስጥ ተጥለው የተገኙ 3 ህጻናት የአንድ እናት ልጆች መሆናቸው በምርመራ ተረጋግጧል
የለንደን ፖሊስ የዘረመል ምርመራውን ተከትሎ የልጆቹን እናት በማፈላለግ ላይ እንደሆነ ተሰምቷል
ባለፉት 7 አመታት በምስራቅ ለንደን በህዝብ መናፈሻ ውስጥ ተጥለው የተገኙ አዲስ የተወለዱ ህጸናት የአንድ እናት ልጆች መሆናቸው በዘረመል ምርመራ ተረጋግጧል።
በ2017 በህዝብ መናፈሻ ውስጥ ተጥሎ የተገኝው ህጻን ሄሪ በ2019 ተጥላ የተገኝችው ህጻን ሮማን እና በዚህ አመት በተመሳሳይ ሁኔታ በፓርክ የተገኝችው ህጻን ኤልሳ አንድ አይነት አጋጣሚን እንጂ አንድ አይነት ወላጅን ይጋራሉ ብሎ የገመተ አልነበረም።
በፈረንጆቹ ታህሳስ 18 ከተወለደች ገና በሰአታት ውስጥ በፓርክ ተጥላ የተገኝች ህጻን መኖሯን የሰማው ፖሊስ ከዚህ ቀደም ከነበሩት አጋጣሚዎች ጋር በማገናኝት በጥርጣሬ ምርመራውን ይጀምራል።
የህጻናቱ ዘረመል በመሰብሰብ የህክምና ምርመራ ያስደረገው ፖሊስ ጥርጣሬው ትክክለኛ ሆኖ ሶስቱ ህጻናት ከአንድ አይነት ቤተሰብ የተገኙ መሆናቸውን አረጋግጧል።
በ2017 እና 2019 ተጥለው የተገኙት ህጻናት በአሁኑ ወቅት በጉድፍቻ ተሰጥተው በተለያዩ ቤተሰቦች ስር እየኖሩ ሲሆን አዲሷ እህታቸው ደግሞ በማደጎ ቤት ትገኛለች።
የለንደን ፖሊስ ወላጆቹን ለማፈላለግ እያደረገ ባለው ጥረት የህጻናቱን ዘረመል በዋና ከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ የፖሊስ ቢሮዎች በማሰራጨት ማህደሮች እያገላበጠ ሲሆን ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ማንኛውም መረጃ ያለው ሰው ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቋል።
ለመጨረሻ ግዜ ተጥላ የተገኝችው ህጻን ሁኔታ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደተወለደች ያሳያል ያሉት የህክምና ባለሙያዎች የሙቀት መጠነኗን እና የልብ ምቷን ለማስተካከል ግማሽ ቀን የፈጀ የህክምና ክትትል እንደተደረገላት ተናግረዋል።
ሶስቱ የአንድ እናት ልጆች አስተዳደግ ምን ሊሆን ይገባል በሚል የተሰየመው የቤተሰብ ጉዳዮች ፍርድ ቤት የዘረመል ምርመራው ውጤት ለህጻናቱ ደህንነት ሲባል በመገናኛ ብዙሀን እንዳይዘገብ ከልከሎ የነበረ ሲሆን ፖሊስ የህጻናቱን ወላጆች ለማፈላለግ በማደርገው ጥረት ያገዘኛል በሚል ዘገባው እንዲሰራጭ በመጠየቁ ጉዳዩ የእንግሊዝ ጋዜጦች መነጋገርያ ሆኗል።
በዩናይትድ ኪንግደም ህጻናትን ጥሎ መሰወር የተለመደ አይደለም በሀገሪቷ በአመት ከ50 ያነሱ ብቻ ህጻናት ተጥለው ይገኛሉ ይህ ሌሎች የአካባቢው ሀገራት ካላቸው ሪከርድ አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል።