የመጨረሻው የሶቬት መሪ ጎርቫቼቭ በ91 አመታቸው ህይወታቸው አለፈ
ምዕራባውያን “የታሪክን ሂደት የለወጠ መሪ” እያሉ በሚያሞካሽዋቸው ጎርባቼቭ ህልፈት ማዘናቸው ገለጹ
ጎርባቼቭ የምዕራብንና የምስራቁ ዓለም ለማቀራረብ በተጫወቱት የመሪነት ሚና የኖቤል ሽልማት አግኝተዋል
ምዕራባውያን “የታሪክን ሂደት የለወጠ መሪ” እያሉ በሚያሞካሽዋቸው ጎርባቼቭ ህልፈት ማዘናቸው ገለጹ፡፡
የመጨረሻው የሶቭየት መሪ ሚካይል ሰርጌይ ጎርባቼቭ በ91 ዓመታቸው ማረፋቸው የተለያዩ የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን የሩሲያ ፕሬዝዳንት ማዕከላዊ ክሊኒካል ሆስፒታል መረጃን ዋቢ በማድረግ በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡
በዚህም የቀድሞ የሶቭየት መሪ ህልፈት ዜናን ተከትሎ የተለያዩ የዓለም መሪዎች የተሰማቸው ሃዘን እየገለጹ ነው፡፡
በጎርቫቼቭ ህልፈት ሃዘናቸውን በመግለጽ ቀዳሚ የሆኑት ሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን መግለጻቸውን ቃል አቀባያቸው ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለሩሲያ የዜና ወኪልሉ ፤ ኢንተርፋክስ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን በጎርባቼቭ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ፤"የነጻ አውሮፓን መንገድ የጠረገ ታማኝ መሪ" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ የቀድሞ የሶቭየት መሪን ገልጸዋቸዋል።
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በበኩላቸው ጎርቫቼቭን “የታሪክን ሂደት የቀየሩ መሪ ነበሩ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባጋሩት ጽሁፍ ለእርሳቸው ያላቸውን ክብር ገልጸዋል።
“ዓለም ቁርጠኛና ለሰላም ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ ታላቅ መሪ አጥታለች”ም ብለዋል ዋና ጸሃፊው፡፡
ጎርባቼቭ በቀዝቃዛው ጦርነት ውጥረት ውስጥ “መጪውን ዘመን አሻግረው መመልከት የቻሉ ልዩ ፖለቲከኛ ነበሩ” ያሉት ደግሞ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ናቸው፡፡
ጆ-ባይደን፤ ጎርባቼቭን “ብርቅዬ መሪ” ሲሉም ጎርባቼቭን ገልጸዋቸዋል፡፡
ሌላው በጎርባቼቭ ህልፈት ሃዘናቸውን የገለጹት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንም፤ የቀድሞ የሶቭየት መሪ “ድፍረት እና ታማኝነት” ተላበሱ ታላቅ መሪ ነበሩ ብለዋል፡፡
"የጎርባቼቭን ሞት ሳውቅ በጣም አዝኛለሁ፤የቀዝቃዛውን ጦርነት ለማቆም ያሳየውን ድፍረት እና ታማኝነት ሁል ጊዜ አደንቃለሁ" ሲሉም ነው ጆንሰን በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ የገለጹት፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም እንዲሁ በጎርባቾቭ ሞት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው እሳቸው “የሰላም ሰው” ነበሩ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ማክሮን አክለውም ጎርባቼቭ “ ለሩሲያውያን የነጻነት መንገድ የከፈተ ነው እንዲሁም ለአውሮፓ ሰላም በነበራቸው ቁርጠኝነት ታሪካችን የቀየሩ መሪ” ሲሉ ያላቸው አድናቆት ገልጸዋል፡፡
የቀድሞ የሶቭየት መሪ ጎርባቸቭ ፣ በሶቭየት ህብረትና በምዕራባውያኑ መካከል ከፍተኛ ውጥረት በነበረበት ወቅት “ቀዝቃዛው ጦርነት” እንዲቆም አቅጣጫ የቀየሱ መሪ ተደርገው የሚታዩ መሪ መሆናቸው ይታወቃል።
በዚህም እንደፈረንጆቹ 1990 በሁለቱም የምዕራብ እና የምስራቅ ካምፖች መካከል የነበረውን ግንኙነት ለመለወጥ በተጫወቱት ከፍተኛ የመሪነት ሚና የኖቤል ሰላም ተሸላሚ ሆነዋል።
ያም ሆኖ ሶቭየት ህብረትን ከመፈራረስ መታደግ ያልቻሉት ጎርባቼቭ፤ ከ30 ዓመታት በፊት ታላቋ ኃያል ሀገር ሶቪየት ሀብረት እስከፈረሰችበት ወቅት ሶሻሊስቷ ሀገር የመጨረሻ ፕሬዝዳንት ሆነው ማገልገላቸውም ይታወሳል፡፡
ጎርባቼቭ የምዕራብንና የምስራቁ ዓለም ለማቀራረብ በተጫወቱት የመሪነት ሚና የኖቤል ሽልማት አግኝተዋል