አሜሪካ ሚሳኤል የታጠቀች ባህርሰርጓጅ መርከብ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ልትክል ነው
ፔንታጎን እስራኤልን ለመጠበቅ የትኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል
የእስራኤል ባለስልጣናት ኢራን ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቷን ተናግረዋል
የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር ሊዩድ ኦስቲን ሚሳኤል የታጠቀች ባህር ሰርጓች መርከብ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለመላክ ትዕዛዝ ሰጡ።
ሚኒስትሩ በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አብርሃም ሊንከን ስም የተሰየመችው “ሊንከን” አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ በፍጥነት ወደ መካከለኛው ምስራቅ እንድትደርስም አዘዋል።
በእስያ ፓስፊክ የምትገኘውና “ዩኤስኤስ ቲወዶር ሩዝቬልት”ን የምትተካው “ሊንከን” በአሁኑ ወቅት የት እንደደረሰች አልተገለጸም።
ፔንታጎን ባህር ሰርጓጅ እና አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቦች በፍጥነት ወደ ቀጠናው እንዲደርሱ ያዘዘው ኢራን በሃማስ የፖለቲካ ቢሮ ሃላፊው ኢስማኤል ሃኒየህ ግድያ ተጠያቂ ባደረገቻት እስራኤል ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው መባሉን ተከትሎ ነው።
የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት ከአሜሪካ አቻቸው ሊዩድ ኦስቲን ጋር ትናንት ማምሻውን በስልክ ምክክር ማድረጋቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
በዚህ ውይይት ወቅት ኦስቲን አሜሪካ “እስራኤልን (ከኢራን ጥቃት) ለመከላከይ የትኛውንም እርምጃ” እንደምትወስድ ተናግረዋል ብለዋል የፔንታጎን ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል ፓት ራይደር።
የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ወደ መካከለኛው ምስራቅ ጉዞ እንድትጀምር ያዘዟት “ዩኤስኤስ ጆርጂያ” ባህር ሰርጓጅ መርከብ ወደ ቀጠናው በምን ያህል ቀን እንደምትደርስ ግን የፔንታጎን ቃልአቀባይ ያሉት ነገር የለም።
አሜሪካ ከጦር መርከቦቿ ባሻገር ተጨማሪ ተዋጊ ጄቶችን በማሰማራት አጋሯን እስራኤልን ሊቃጣባት ከሚችለው ጥቃት ለመመከት እየሰራች መሆኑን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧ።
የኢራን ብሄራዊ ቴሌቪዥን ከትናንት በስቲያ ከእይታ ተሰውሮ ጥቃት የሚፈጽም ሚሳኤልን ጨምሮ በእስራኤል ላይ “ከባድ ቅጣት” ለማድረስ የተዘጋጁ መሳሪያዎችን የሚያሳይ ምስል ለቋል።
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ምክትል አዛዥም በቴል አቪቭ ላይ የበቀል እርምጃውን ለመፈጸም የጠቅላይ መሪውን አያቶላህ አሊ ሃሚኒ ትዕዛዝ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ቴህራን ከሁለት ሳምንት በፊት የተገደለውን ኢስማኤል ሃኒየህ ደም ለመበቀል እወስደዋለሁ ያለችውን እርምጃ ለመመከት እስራኤል በብርቱ ዝግጅት ስታደርግ ቆይታለች።