ፑቲን በመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ጉዳይ ከፍልስጤሙ መሪ አባስ ጋር ሊነጋገሩ ነው
አባስ ከሞስኮ ቆይታቸው በኋላ ፕሬዝዳንት ታይፕ ኢርዶጋን ጋር ለመነጋገር ወደ ቱርክ ያቀናሉ ተብሏል።
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ በቀጣናው ከፍተኛ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ተፈጥሯል
ፑቲን በመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ጉዳይ ከፍልስጤሙ መሪ አባስ ጋር ሊነጋገሩ ነው።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ብላድሚር ፑቲን በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረውን ቀውስ በተመለከተ ከፍልስጤሙ ፕሬዝደንት መሀሙድ አባስ ጋር በዛሬው እለት በሞስኮ እንደሚነጋገሩ ክሬሚሊን አስታውቋል።
"የፍልስጤም-እስራኤል ግጭት እየተባበሰ ስላለበት የመካከለኛው ምስራቅ አሁናዊ ሁኔታ እና በጋዛ ሰርጥ ስላለው አስከፊ የሰብአዊ ቀውስ ሁኔታ ሀሳብ ይቀያየራል ተብሎ ይጠበቃል" ብሏል ክሬሚሊን።
አባስ እስከ ረቡዕ ድረስ በሞስኮ እንደሚቆዩ እና ከዚያ በኋላ ከፕሬዝዳንት ታይፕ ኢርዶጋን ጋር ለመነጋገር ወደ ቱርክ እንደሚያቀኑ ሮይተርስ ዘግቧል።
ከኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ እና የሳኡዲው ልኡል አልጋወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ጨምሮ ከአረብ መሪዎች ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት ሩሲያ፣ በቅርቡ ቴህራን ውስጥ በሀማስ የፖለቲካ መሪ ሀኒየህ ላይ የተፈጸመውን ግድያ አውግዛለች። ሩሲያ ሁሉም አካላት መካከለኛው ምስራቅን የበለጠ አለመረጋጋት ውስጥ ከሚከት ተግባራት እንዲቆጠቡም ጥሪ አድርጋለች።
ምዕራባውያን በ1967 ስምምነት መሰረት ፍልስጤም ራሷን የቻለች ሀገር እንዳትሆን ችላ ብለዋል ስትል ሩሲያ በተደጋጋሚ ትችት አቅርባለች።
በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የሀማስ መሪ ሀኒየህ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን በአዲሱ የኢራን ፕሬዝደንት ፔዝስሽኪያኒ በዓለ ሲመት ላይ ከታደመ በኋላ ባረፈበት ክፍል እና የሄዝቦላ ወታደራዊ አዛዥ ሹክር ደግሞ በቤሩት ከተማ ዳርቻ መገደላቸውን ተከትሎ ነው።
ሀማስ እና ኢራን ግድያውን ፈጽማለች በሏት እስራኤል ላይ የበቀል እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል። በሹክር ላይ ለተፈጸመው ግድያ ወዲያውኑ ኃላፊነት የወሰደችው እስራኤል፣ ሀኒየህን መግደሏንም ቆየት ብላ አምናለች።
ኢራን በእስራኤል ላይ ጥቃት የምትሰነዝር ከሆነ በቀጣናው ከፍተኛ ግጭት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።