የአሜሪካ “ቢ-1ቢ” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በኮሪያ ልሳነ ምድር ደጋግሞ የሚበረው ለምንድን ነው?
ስሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ባስወነጨፈች ማግስት አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የአየር ልምምድ ጀምረዋል
“ቢ-1ቢ” በ2024 አራት ጊዜ በኮሪያ ልሳነ ምድር መብረሩን ደቡብ ኮሪያ ገልጻለች
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን የሶስትዮሽ የአየር ልምምድ ጀምረዋል።
ሀገራቱ በዛሬው እለት ልምምዱን የጀመሩት ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ሀሙስ “ሃውሶንግ 19” የተሰኘውን ግዙፍ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ከአንድ አመት በኋላ ማስወንጨፏን ተከትሎ ነው።
አሜሪካን መምታት ይችላል የተባለው “ሃውሶንግ 19” በበረራ ከፍታው እና ቆይታው ከእስካሁኑ ሙከራ የተሻለ ሆኖ መገኘቱ ዋሽንግተን እና የቀጠናው አጋሮቿን ሴኡል እና ቶኪዮ አሳስቧል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ግን ሚሳኤሉ በተቀናቃኞቻችን ለተደቀነብን የደህንነት ስጋት ወሳኝ ነው ብለውታል።
ከነገ በስቲያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የምታካሂደው አሜሪካ ግዙፉን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኗን በመላክ ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር የአየር ልምምድ በማካሄድ ቁጣዋን ገልጻለች።
ሶስቱ ሀገራት በ2024 በርካታ የጦር ልምምድ ያደረጉ ሲሆን፥ የዛሬውን አይነት ግዙፍ የአየር ልምምድ ሲያደርጉ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
የዋሽንግተን “ቢ-1ቢ” ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በኮሪያ ልሳነ ምድር መብረሩም ሶስቱ ሀገራት ለሰሜን ኮሪያ ተጠባቂ ጥቃት ያላቸውን ዝግጁነት ለማሳየት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው አሜሪካ “ቢ -1ቢ” ቦምብ ጣይ አውሮፕላኗን በኮሪያ ልሳነ ምድር ዙሪያ እና አቅራቢያ በዚህ አመት አራት ጊዜ አብርራለች።
24 ኒዩክሌር ቦምቦችን መሸከም የሚችለው “ቢ -1ቢ” አውሮፕላን ነዳጅ ለመሙላት ሳያርፍ 7 ሺህ 400 ኪሎሜትሮችን መብረር የሚችል ነው።
ቦምብ ጣይ አውሮፕላኑ ከ84 በላይ 227 ኪሎግራም የሚመዝኑ ኮንቬንሽናል ቦምቦችን በመሸከም እንዳሻው እየተገለባበጠ ለረጅም ሳአት ጥቃት ማድረስ መቻሉም ለውጭ ሀገር ግዳጆች ቀዳሚ ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል።
ሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ሙከራ ባደረገች ማግስት ከደቡብ ኮሪያ ጋር ወታደራዊ ልምምድ የምታደርገው አሜሪካ ከአውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦች ባሻገር “ቢ -1ቢ” ቦምብ ጣይ አውሮፕላኗን ወደ ኮሪያ ልሳነ ምድር እየላከች ለሰሜን ኮሪያ የማስጠንቀቂያ መልዕክት እየሰደደች ነው።
ፒዮንግያንግ በበኩሏ የዋሽንግተን፣ ሴኡልና ቶኪዮን ልምምድ የወረራ ዝግጅት ነው በሚል በመቃወም የሚሳኤል ሙከራዋን ስትገፋበት በተደጋጋሚ ታይቷል።
በዛሬው እለት የአሜሪካው “ቢ-1ቢ” አውሮፕላን እየተሳተፈበት ለሚገኘው የሶስትዮሽ የአየር ልምምድ የምትሰጠው ምላሽም ይጠበቃል።