የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለምን ማክሰኞ ዕለት ብቻ ይካሄዳል?
ሀገሪቱ በየ አራት ዓመቱ አንዴ ሕዳር ወር ላይ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ስታካሂድ 179 ዓመታትን አስቆጥራለች
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሁሌ የመጀመሪያ ማክሰኞ ዕለት እንዲካሄድ አስገዳጅ ህግ አላት
የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለምን ማክሰኞ ዕለት ብቻ ይካሄዳል?
የዓለማችን ልዕለ ሀያል ሀገር አሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሊካሄድ አምስት ቀናት ብቻ ቀርቶታል።
በሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ እና ዲሞክራቷ ካማላ ሀሪስ መካከል የሚካሄደው ይህ ምርጫ የፊታችን ማክሰኞ ይካሄዳል።
አሜሪካ በየ አራት ዓመቱ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት፣ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ምርጫን አንዴ ታካሂዳለች።
ይህ ምርጫ ከፈረንጆቹ 1845 ጀምሮ በመካሄድ ላይ ሲሆን ምርጫው ሁልጊዜ ማክሰኞ ዕለት ብቻ ይካሄዳል።
በሀገሪቱ ምርጫ ህግ መሰረት ምርጫው በየ አራት ዓመቱ ህዳር ወር ላይ በመጀመሪያው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ብቻ እንዲካሄድ የሚያስገድድ ህግ አላት።
ምርጫው የሚካሄድበት ሕዳር ወር እና ማክሰኞ ዕለት እንዲሆን የተመረጠው ደግሞ የምርጫ ማስፈጸሚያ ህጉ በወጣበት ጊዜ በአብዛኛው የአሜሪካ አካባቢዎች ማክሰኞ ዕለት ገበያ ስላለ እና ህዝቡ በአንጻራዊነት እረፍት የሚያደርግበት ዕለት ነው በሚል እሳቤ ነበር።
በአብዛኛው የዓለማችን ሀገራት ምርጫዎች የሚካሄዱት ዕሁድ ዕለት ሲሆን በአሜሪካ ይህ ዕለት የድምጽ መስጫ ቀን ያልተደረገው በወቅቱ አብዛኛው አሜሪካዊ ዕሁድ ዕለትን ለአምልኮ ብቻ የማዋል ልምድ ስለነበረው እንደሆነበኖርዝ ኢስተርን ዩንቨርስቲ የታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ጀሲካ ሊንከር ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሕዳር ወር ድምጽ የሚሰጥበት ወር ሆኖ የተመረጠው አብዛኛው አሜሪካዊ ይህን ወቅት ሰብሉን አስቀድሞ ስለሚሰበስብ እና ያገሬው ገበሬ የተሻለ የዕረፍትጊዜ የሚያገኝበት ወቅት ስለሆነ ነበር።
አሜሪካዊያን አሁን ያለው ህይወት የምርጫ ህጉ ከወጣበት ጊዜ ሲነጻጸር በብዙ መልኩ ለውጥ ያለ ቢሆንም የሀገሪቱን ታሪክ ላለማጥፋት ሲባል ህጉ ባለበት እንዲቀጥል ተደርጓል።
በዘንድሮው ምርጫ ላይ ዋነኛ ተፎካካሪ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ እና ካማላ ሀሪስ ፉክክሩን የቀጠሉ ሲሆን ታዋቂ ሰዎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችም በምረጡኝ ቅስቀሳው ላይ እየተሳተፉ ናቸው።
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኢለን መስክ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ ሲሆኑ እንደ ቴይለር ስዊፍት፣ ቢዮንሴ እና ሊኦናርዶ ዲካፕሪዮ ደግሞ የካማላ ሀሪስ ደጋፊ መሆናቸውን በይፋ አውጀዋል።