እስራኤል ከ1 ሚሊየን በላይ የሰሜናዊ ጋዛ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ አሳሰበች
የእስራኤል ጦር ከሃማስ ጋር የምድር ውጊያ ለመጀመር ነው ፍልስጤማውያን ከከተማዋ እንዲወጡ የ24 ስአት ጊዜ የሰጠው
የመንግስታቱ ድርጅት ግን ፍልስጤማውያንን በአንድ ቀን ከጋዛ ለማስወጣት መታሰቡ አደገኛ ቀውስ ያስከትላል ብሏል
ፍልስጤማውያን ከሰሜናዊ የጋዛ ክፍል ወደ ደቡቡ በስፋት እየፈለሱ መሆኑ ተነገረ።
እስራኤል ከ1 ሚሊየን በላይ የሰሜናዊ ጋዛ ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቧን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከከተማዋ እየወጡ ነው።
ፍልስጤማውያኑ በተሽከርካሪዎች እና በእግራቸው ከተማዋን ለቀው እየወጡ መሆኑን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
በትናንትናው እለት ከከተማዋ በተሽከርካሪ ሲወጡ የነበሩ 70 ሰዎች በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደላቸውንም ነው ሃማስ የገለጸው።
እስራኤል በጋዛ ውስጥ የሚገኙ የሃማስ ይዞታዎችን ለመደብደብና ታጣቂ ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ የምድር ውጊያ ልትጀምር ተዘጋጅታለች።
በዚህም ንጹሃን እንዳይጎዱ በሚል ፍልስጤማውያን ከሰሜናዊ ጋዛ እንዲወጡ 24 ስአት ሰጥታለች።
የመንግስታቱ ድርጅት ሚሊየኖች ተጠጋግተው ከሚኖሩበት ከተማ በአንድ ቀን ይውጡ መባሉ አደገኛ ነው ያለው የመንግስታቱ ድርጅት ቴል አቪቭ ውሳኔዋን ዳግም እንድታጤን አሳስቧል።
ግብጽም ውሳኔው ንጹሃንን ለመጠበቅ ያለመ ሳይሆን ፍልስጤማውያንን ከጋዛ በማስወጣት ወደ ደቡብ ማለትም ወደ ግብጽ ድንበር ለመግፋት የተጠነሰሰ ነው በሚል ተቃውማዋለች።
ሃማስም ፍልስጤማውያን የትም ቢሄዱ ከእስራኤል ጥቃት ስለማያመልጡ ከጋዛ እንዳይወጡ ነው ያሳሰበው።
አንድ ሳምንት በደፈነው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት እስካሁን ከ1 ሺህ 900 በላይ ፍልስጤማውያን እና ከ1 ሺህ 300 በላይ እስራኤላውያን ህይወት አልፏል፤ ከ1 ሺህ 500 በላይ የሃማስ ታጣቂዎች መገደላቸውንም የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
“ሃማስን እናጠፋዋለን” ያሉት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፥ የእስካሁኑ የአየር ድብደባ “ገና ጅማሮ ነው” ማለታቸውም የጋዛ ቀጣይ እጣ ፈንታን አሳሳቢ አድርጎታል።