ዩክሬን ጦርነቱን በተናጠል ካቆመች ትፈራርሳለች - የላቲቪያ ጠቅላይ ሚኒስትር
ጠቅላይ ሚኒስትር ክርሲያንስ ካርፒንስክ ጎረቤቷ ኬቭ ከሩሲያ ጋር ስለገባችበት ጦርነት ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ አድርገዋል
የአውሮፓ ህብረት፣ የደቡብ አሜሪካ እና ካሪቢያን ሀገራት ጉባኤ በቤልጂየም ተካሂዷል
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ ያተኮረውና ከ60 በላይ ሀገራት መሪዎች የተሳተፉበት አለማቀፍ ጉባኤ በቤልጂየም መዲና ብራሰልስ ተካሂዷል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን ከአል ዐይን ኒውስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዩክሬን ጎረቤት ከሆነችው ላቲቪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክርሲያንስ ካርፒንስክ የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት የመቆሙ ጉዳይ በሞስኮ እጅ ነው ብለዋል።
ሁለቱ ሀገራት ያልተመጣጠነ ሃይል ያላቸው ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ክርሲያንስ፥ ኬቭ በተናጠል ጦርነቱን ካቆመች የመፈራረሷ ጉዳይ አይቀሬ መሆኑን ነው የገለጹት።
የአውሮፓ ህብረት ሁለቱም ተፋላሚ ሀገራት በእኩል ደረጃ በመመልከት ሁለቱም ሀገራት ጦርነቱን እንዲያቆሙ ቢጠይቅም ኬቭ ቀድማ በተናጠል ውሳኔ ላይ ከደረሰች አደገኛ ችግር ይገጥማታልም ብለዋል።
“ጦርነቱ በቀድሞ ቅኝ ገዥ እና ቅኝ ተገዥ ሀገራት መካከል መሆኑን መዘንጋት የለብንም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የብራሰልሱ ስብሰባ ይህንኑ ጉዳይ ለደቡብ አሜሪካና ካሪቢያን ሀገራት ለማስረዳት ማገዙንም አብርተዋል።
በጦርነቱ ምክንያት የአለም የምግብ ዋጋ መናሩን በማንሳትም በተለይ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በዚህ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ጠቁመዋል።
በመሆኑም ሀገራቱ ሞስኮን ከማውገዝ ባለፈ ለኬቭ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል ነው ያሉት።
የላቲን አሜሪካ ሀገራት በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ዙሪያ ከአውሮፓ ህብረት በተቃርኖ መቆማቸው ይታወቃል።
ከ2015 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው የብራሰልሱ ምክክርም የሀገራቱን መሪዎች አቋም ለማስለወጥ ያለመ ነበር ተብሏል።