ተጠባቂው የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት በካርቱም
ሩሲያ እና ሱዳን በፖርት ሱዳን ወታደራዊ ማዘዣ ለመገንባት ያደረጉት ስምምነት ዋነኛ የውይይት አጀንዳ ይሆናል ተብሏል
ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ከዶላር ውጪ ለመገበያየት በማግባባት ላይ ትገኛለች
የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ላቭሮቭ ሱዳንን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት አፍሪካን ጎብኝተው የተመለሱት የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጊ ላቭሮቭ ዳግም ወደ አፍሪካ ተመልሰዋል፡፡
በአሁኑ ጉብኝታቸውም ከምዕራባዊያን ጋር ሆድና ጀርባ የሆነችው ማሊን እና ማዕከላዊ አፍሪካን የጎበኙ ሲሆን አሁን ደግሞ ጎረቤት ሀገር ሱዳንን በመጎብኘት ላይ ናቸው፡፡
ሰርጊ ላቭሮቭ በካርቱም በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታቸውም ከሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
በፈረንጆቹ 2017 ላይ ሱዳን ከሩሲያ ጋር የፈጸመችው ወታደራዊ ማዘዣ ትግበራ ጉዳይ የውይይታቸው ዋነኛ አካል እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በዚህ የሁለቱ ሀገራት ስምምነት መሰረት ሩሲያ በቀይ ባህሯ ፖርት ሱዳን ላይ ወታደራዊ ማዘዣ የምትገነባ ሲሆን በካርቱም የተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ግን ይህ ስምምነት እስካሁን እንዳይተገበር እንቅፋት መፍጠሩ ተገልጿል፡፡
የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች የቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አልበሽር ከሩሲያ ጋር የተፈራረሙት ስምምነትን ጥናት እያደረጉበት እንደሆነ ቢናገሩም አሜሪካ ይህ ስምምነት እንዳይተገበር ጫና መፍጠሯን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ፡፡
ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን ተሳትፎ ለማጠናከር ፍላጎት ማሳየቷን ተከትሎም በፖርት ሱዳን ላይ ለመገንባት ያሰበችውን ወታደራዊ ማዘዣ ለመተግበር ከሱዳን መሪዎች ጋር ለመወያየት የሞስኮ ከፍተኛ መሪ ወደ ካርቱም ተጉዘዋል፡፡
የሰርጊ ላቭሮቭ ሌላኛው የጉዞ ዓላማ የፊታችን ሀምሌ ወር በሩሲያዋ ሱቺ የወደብ ከተማ ላይ በሚካሄደው ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሱዳን እንድትሳተፍ ለማግባባት እንደሆነም ታስ ዘግቧል፤፡
ሩሲያ በዚህ ጉባኤ ላይ ሁሉንም የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች እንደምትጋብዝ የገለጸች ሲሆን የጉባኤው አላምም ሩሲያ ከአፍሪካ ጋር ከዶላር ውጪ በሆነ ገንዘብ ለመገበያየት ስምምነት ላይ መድረስ ዋነኛው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሰርጊ ላቭሮቭ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ አፍሪካ መጥተው ኤርትራን፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ኢስዋትኒ እና ሌሎች ሀገራትን ጎብኝተው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡