የአሜሪካ እና ሩሲያ ከፍተኛ ባለስልጣናት አፍሪካን በተመሳሳይ ወቅት እየጎበኙ ናቸው
የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጊ ላቭሮቭ ኤርትራ ገቡ።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገባችበትን ጦርነት ተከትሎ በአሜሪካ እና ምዕራባዊያን የደረሰባትን መገለል ለማካካስ ከተቀረው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስቀጠል ጥረት ላይ ትገኛለች።
ለዚህ ሲባልም የሩሲያ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጊ ላቭሮቭ ወደ አፍሪካ ከመጡ ዛሬ አራተኛ ቀናቸውን ይዘዋል።
- የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀገራቸው ከዩክሬን ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት ዙሪያ ለኤርትራ ገለፃ አደረጉ
- የኤርትራው ፕሬዝዳንት “የምዕራባውያን ፖለሲ ዓለም አቀፍ ቀውስ እያስከተለ ነው” አሉ
ውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ የመጀመሪያ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ያደረጉ ሲሆን በጋራ ወታደራዊ ልምምድ፣ በንግድ እና ብሪክስ የተባለው የአምስት የዓለማችን ሀገራት ስብስብ የራሱን መገበያያ ገንዘብ ስለመቅረጽ ተወያይተዋል።
አንጎላ ሌላኛዋ በሰርጊ ላቭሮቭ የተጎበኘች የአፍሪካ ሀገር ስትሆን ሁለቱ ሀገራት በነዳጅ ቴክኖሎጂ እና ማዕድን ልማት በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል ተብሏል።
አሁን ደግሞ ከዓለም ዲፕሎማሲ ወደ ተገለለችው ኤርትራ የገቡት ሰርጊ ላቭሮቭ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩ ይጠበቃል ሲል ራሺያ ቱዴይ ዘግቧል።
ኤርትራ እና ሩሲያ ከዚህ በፊት ወታደራዊ ስምምነቶችን የተፈራረሙ ሲሆን ሞስኮ በአፍሪካ ቀንዷ ኤርትራ ወታደራዊ ሰፈሮችን መገንባት እንደምትፈልግ ተዘግቧል።
ሩሲያ በሱዳን የቀይ ባህር ዳርቻ ላይ ወታደራዊ ማዘዣ ለመገንባት ከቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት አልበሽር የአስተዳድር ዘመን ከስምምነት ላይ ደርሰው የነበረ ሲሆን በሱዳን የፖለቲካ አለመረጋጋት መከሰቱን ተከትሎ እና በአሜሪካ ጫና ምክንያት ስምምነቱ እስካሁን አልተጀመረም።
አሜሪካም ሁለት ጉምቱ ባለስልጣናቷን ወደ አፍሪካ የላከች ሲሆን በተመድ የዋሽንግተን አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ እና የግምጃ ቤት ሚንስትሯ የአፍሪካ ሀገራትን በመጎብኘት ላይ ናቸው።