“ምዕራባውያን አለም በነሱ ስግብግብ ፍላጎትና ህግ ብቻ እንዲመራ እያስገደዱ ነው” - ላቭሮቭ
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ አሜሪካና ምዕራባውያንን “የውሸት ስርወ መንግስት” ብለዋቸዋል
በዩክሬን የቀረበውን ባለ10 ነጥብ የሰላም እቅድም “ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል” በሚል ውድቅ አድርገውታል
አሜሪካ እና ምዕራባውያን እየከሰመ ያለውን የባለአንድ ወገን አለማቀፍ ስርአት ለማስቀጠል ጦርነት ማቀጣጠልን ተያይዘውታል ስትል ሩሲያ ወቅሳለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፥ “የውሸት ስርወ መንግስት” ሲሉ የገለጿቸው ምዕራባውያን ሁሉንም ወገን በእኩል አይን የሚመለከት ባለብዙ ወገን የአለም ስርአት እንዳይፈጠር የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው ብለዋል።
“ምዕራባውያን አለም በነሱ ስግብግብ ፍላጎትና ህግ ብቻ እንዲመራ እያስገደዱ ይገኛሉ” ሲሉም ነው የተናገሩት።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በ1991 ሶቪየት ህብረት የፈራረሰችበትን መንገድ እና በአሁኑ ወቅትም ለዩክሬን ቢሊየን ዶላሮችን በመለገስ እየተደረገ ነው ያሉትን “ቅይጥ ጦርነት” በስፋት ቢያብራሩም ስለወቅታዊው የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ሂደት በንግግራቸው አላካተቱም።
ላቭሮቭ ከተመድ ጠቅላላ ጉብኤ ንግግራቸው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “አሜሪካ ዩክሬንን በመጠቀም ከሩሲያ ጋር በቀጥታ እየተፋለመች ነው” ብለዋል።
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የመስፋፋት እቅድንም አውግዘዋል።
እንደ ብሪክስ ያሉ ቡድኖችን የሚቀላቀሉ ሀገራት መበራከት “የትኛውም ሀገር በሆነ ሃይል ፍላጎት ብቻ መመራት እንደሰለቸው ማሳያ ነው” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
“ፍትሃዊ ጥቅምና ስልጣኔን የሚሹ በርካቶች የራሳቸውን ጥቅምና ልዕልና ባስቀደሙና የቅኝ ግዛት እሳቤ ባላቸው ጥቂቶች መካከል የሚደረገው ፍልሚያ የአለምን ቀጣይ መጻኢ ይወስናል” ያሉት ሰርጌ ላቭሮቭ የመንግስታቱ ድርጅትም ራሱን እንዲመለከት አሳስበዋል።
የላቭሮቭን ንግግር በአዳራሽ ውስጥ ያልተከታተሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ ከአራት ቀናት በፊት ባደረጉት ንግግር ሩሲያ “ምግብ፣ ነዳጅ ብሎም የዩክሬን ህጻናትን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመች ነው” የሚል ወቀሳ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ዩክሬንን አለመደገፍ በአለም ላይ ነጻ ሀገር እንዳይኖር እንደመፍቀድ ይቆጠራል ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ አስታውሷል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭን አሜሪካ እና ምዕራባውያንን በወቀሱበት ንግግራቸው 19 ወራት ያስቆጠረውን ጦርነት ለማስቆም በዜለንስኪ በኩል የቀረበውን ባለ10 ነጥብ የሰላም እቅድ ውድቅ አድርገዋል።
ምዕራባውያን ለሞስኮ የገቡትን ቃል (በሩሲያ ታንኮች ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ለማንሳትና ከአለም የስዊፍት ስርአት ጋር ማገናኘት) ስላልፈጸሙም ሀገራቸው ወደ ጥቁር ባህር የእህል ስምምነት እንደማትመለስ ነው ያነሱት።