የአውሮፓ ህብረት በሩሲያውያን ባለጸጋዎች ላይ የጣለውን ማዕቀብ አነሳ
እግዱ የተነሳላቸው የሩሲያ ባለጸጋዎች ለፕሬዝዳንት ፑቲን የቅርብ ሰዎች ናቸው ተብሏል
የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት ሩሲያ ማሸነፏ አይቀሬ ነው ብለዋል
የአውሮፓ ህብረት በሩሲያውያን ባለጸጋዎች ላይ የጣለውን ማዕቀብ አነሳ፡፡
ለአንድ ሳምንት ልዩ ዘመቻ በሚል የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ከ560 ቀናት በላይ አስቆጥሯል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች ሀገራት በሩሲያ ላይ ከ12 ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ብቻውን ከ1ሺህ 600 በላይ ሩሲያዊያን ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን በተወሰኑት ላይ ማዕቀቤን አንስቻለሁ ብሏል፡፡
ለፕሬዝዳንት ፑቲን እና መንግስታቸው ድጋፍ ያደርጋሉ ተብለው የተለዩ ሩሲያዊያን ባለጸጋዎች ገንዘባቸው እና ሌሎች ንብረቶቻቸው እንዳይንቀሳቀሱ ታግደው ቆይተዋል፡፡
ይሁንና ህብረቱ ሶስት የናጠጡ ሩሲያዊያን ንብረቶች ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ እንዳነሳ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ከሆነ እገዳው የተነሳላቸው ባለጸጋዎች ለሩሲያ መንግስት ቅርብ የሆኑ ናቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ናቸው፡፡
በአውሮፓ ህብረት እገዳው የተነሳላቸው ሩሲያዊያን ባለጸጋዎች መካከል ግሪጎሪ በረዝኪን፣ ፋርካድ አክመዴቭ እና አሌክሳንደር ሹልጊን ተጠቅሰዋል፡፡
ከነሄሊኮፕተሩ ወደ ዩክሬን በመግባት የከዳው ሩሲያዊ የ500 ሺህ ዶላር ሽልማት ሊሰጠው ነው
ህብረቱ እገዳውን ያነሳው ባለጸጋዎቹ በተደጋጋሚ እግዱ እንዲነሳላቸው ጉዳዩን ወደ ህግ በመውሰዳቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡
እገዳው የተነሳላቸው ባለጸጋዎች በሚዲያ ኢንዱስትሪ፣ በዩራኒየም ንግድ እና በጋዝ ንግድ ሰፊ ልምድ እና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሀብቶች ያሏቸው ናቸው ተብሏል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም ሩሲያን የጎበኙት የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን ሩሲያ ድል ማድረጓ አይቀሬ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከሩሲያ አቻቸው ጋር በጦር መሳሪያ፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ምግብ ዋስትና ዙሪያ እንደተወያዩ የተገለጸ ሲሆን የጋራ ስምምነቶች እስካሁን ይፋ አልሆኑም ተብሏል፡፡
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ የሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ መሪዎች ውይይት እንዳሳሰባት ገልጻ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ዙሪያ እንዲወያይበት ጠይቃለች፡፡